ፈልግ

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “ሐዋርያዊ መረዳትን የሚያለዝቡ ነገሮች”

አንዳንድ “ሕጋዊ ያልሆኑ” ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ እነዚህን ሁኔታዎች በተለየና በበቂ ሁኔታ የመረዳትን አስፈላጊነትና ብቃት በተመለከተ፣ የወንጌል ሐሳብ በማናቸውም መንገድ እንዳይጣስ ምንጊዜም መጤን ያለበት አንድ ነገር አለ። ቤተክርስቲያን ምክንያቶችንና ሁኔታዎችን ለማለዘብ የሚረዳ ጠንካራ የማሰላሰል ብቃት አላት። ስለዚህ፣ ‹‹ሕጋዊ ያልሆኑ›› ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ከእንግዲህ በከባድ ኃጢአት ውስጥ ይኖራሉ፣ የሚያጸድቅ ጸጋም አጥተዋል ማለት አይቻልም። እዚህ ላይ ሕጉን ካለማወቅ የበለጠ ነገር አለ። አንድ ሰው ሕጉን ሙሉ በሙሉና በሚገባ ሊያውቅ ቢችልም፥ “በውስጡ ያሉ እሴቶችን” የማወቅ ትልቅ ችግር አለበት፤ አሊያም ከዚህ በተለየ መልኩ እንዳያደርግና ወደ ተጨማሪ ኃጢአት ውስጥ ሳይገባ እንዳይወስን በሚከለክል ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሊሆን ይችላል። የሲኖዶሱ አባቶች እንዳስቀመጡት፣“የመወሰን ችሎታን የሚገድቡ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ”። ቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ራሱ እንደተረዳው፣ አንድ ሰው ጸጋና ፍቅር ቢኖረውም፣ ከበጎ ምግባራት አንዱንም ተግባራዊ ላያደርግ ይችላል፤ በሌላ አነጋገር፣ አንድ ሰው በውስጡ ግብረ ገባዊ ትሩፋቶች ቢኖሩትም፣ ከእነዚህ አንዱም ቢሆን በውስጡ መኖሩን በግልጽ ላያሳይ ይችላል፤ ምክንያቱም፣ ያንን በጎ ምግባር አውጥቶ መተግባር ከባድ ነው። “አንዳንድ ቅዱሳን የመልካም ምግባራት ልምዶች ቢኖሩአቸውም፣ እነዚያን በጎ ምግባራት የመተግበር ችግር እስካለባቸው ድረስ፣ አንዳንድ በጎ ምግባራት እንደሌሉዋቸው ይነገራል”።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እነዚህን ምክንያቶች በግልጽ ይጠቅሳቸዋል፡- “ለአንድ ድርጊት ተጠያቂነትና ኃላፊነት ማጣት በአላዋቂነት፣ በስህተት፣ በግዴታ፣ በፍርሃት፣ በልማድ፣ በገደብ የለሽ ግንኙነት፣ እና በሌሎች ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ምክንያቶች ሊደበዝዝ አሊያም ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል”። በሌላ አንቀጽ ላይ ደግሞ ግብረ ገባዊ ኃላፊነትን የሚያለዝቡ ሁኔታዎችን እንደገና ያነሣል፤ “በስሜት ያለመብሰልን፣ የልምድ ጫናን፣ የጭንቀት ወይም ሌሎች ግብረ ገባዊ ተወቃሽነትን የሚቀንሱ ወይም የሚያመነምኑ ሁኔታዎችን” (344) የትምህርተ ክርስቶስ መጽሐፍ በስፋት ይጠቅሳል። በዚህ ምክንያት፣ ስለ አንድ ተጨባጭ ሁኔታ ያለ አሉታዊ አስተሳሰብ የአንድን ሰው ተጠያቂነት ወይም ተወቃሽነት አያመለክትም።

በዚህ እምነት ላይ በመመርኮዝ፣ ብዙዎቹ የሲኖዶሱ አባቶች ሊያረጋግጡ የፈለጉት የሚከተለው ሐሳብ ተገቢ ነው ብዬ እገምታለሁ፡- “በአንዳንድ ሁኔታዎች ሰዎች በተለየ መልኩ መሥራት ከባድ ይሆንባቸዋል። ስለዚህ፣ አጠቃላይ ሕጉን ጠብቆ፣ ከአንዳንድ ድርጊቶች ወይም ውሳኔዎች አኳያ የሚወሰድ ኃላፊነት በሁሉም ረገድ ተመሳሳይ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ሐዋርያዊ ግንዛቤ የአንድን ሰው በሚገባ የታነጸ ኅሊናን ግምት ውስጥ ከማስገባት ባሻገር፣ ለእነዚህ ሁኔታዎችም ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። የተወሰዱ እርምጃዎች የሚያስከትሉአቸው ውጤቶችም ቢሆኑ ሁሌም ተመሳሳይ አይደሉም”።

እኛም እነዚህን የመሰሉ ተጨባጭ ምክንያቶችን ተጽዕኖ ከመገንዘብ በተጨማሪ፣ ግላዊ ንቃተ ኅሊና እኛ ስለ ጋብቻ ያለንን መረዳት በተጨባጭ የማያሳዩ፣ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች የሚንጸባረቁ የቤተክርስቲያን የአሠራር ልምዶችን በተሻለ ሁኔታ ማካተት አለበት እንላለን። በተፈጥሮ፣ ማንኛውም ጥረት የነቃ፣ የታነጸና ኃላፊነትና ጠንካራ ማስተዋል ባለው ጳጳስ የሚመራ፣ ኅሊናን የሚያዳብርና በእግዚአብሔር ጸጋ በይበልጥ መተማመንን የሚያበረታታ መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ኅሊና አንድ የተወሰነ ሁኔታ ከአጠቃላይ የወንጌል ፍላጎት ጋር በተጨባጭ ሊመሳሰል እንደማይችል ከመገንዘብ በላይ ያውቃል። ለጊዜው ለእግዚአብሔር ሊሰጥ የሚችል የልግስና ምላሽ ይህ መሆኑን በሐቅና በታማኝነት ይገነዘባል፤ ሰው ተጨባጭና ውስብስብ ገደቦች ቢኖሩትም ዋና ዓላማው ሙሉ በሙሉ ይህ ባይሆንም፣ እግዚአብሔር ራሱ የሚጠይቀው ይህን መሆኑን በተወሰነ ግብረ ገባዊ እርግጠኝነት ይቀበላል። እኛም በማናቸውም ሁኔታ፣ ይህ መረዳት ቀጣይነት እንዳለው፣ አዳዲስ የዕድገት ደረጃዎችንና  ዓላማው ይበልጥ እውን እንዲሆን የሚያግዙ አዳዲስ ውሳኔዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንዳለበት እናስታውስ።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 301-303 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

26 Jul 2025, 17:07