የዓለም የካቶሊክ ሴቶች ኦብዘርቫቶሪ በመላው አፍሪካ የሰው ልጆችን ህይወት ለማሻሻል አመርቂ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዓለም የሴቶች ኦብዘርቫቶሪ (WWO) በ 2013 ዓ.ም. በዓለም የካቶሊክ የሴቶች ድርጅቶች ማህበር (WUCWO) አማካይነት የተቋቋመ ሲሆን፥ ለሴቶች በተለይም “የማይታዩ” የሚመስሉ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ትኩረት እንዲያገኙ እና ለአጠቃላይ እድገታቸው የሚጠቅሙ ለውጦችን ለማበረታታት እና ለመፍጠር ታልሞ እንደተቋቋመ ተገልጿል።
በዓለም ካቶሊካዊ የሴት ድርጅቶች ማህበር (WUCWO) ሥር ሆኖ የሚንቀሳቀሰው የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት (WWO) ዓላማ አድርጎ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል፣ ብዙውን ጊዜ ድምጽ ለሌላቸው ሴቶች ድምጽ በመሆን፥ በተለይም ደካማ እና የተገለሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚኖሩትን ሴቶች ድምጽ ለማጉላት እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
እ.አ.አ. በ 1910 ዓ.ም. የተመሰረተው የዓለም የካቶሊክ የሴቶች ድርጅቶች ማህበር በዓለም ዙሪያ ከ100 በላይ የካቶሊክ የሴት ድርጅቶችን የሚወክል ሲሆን፥ ከ8 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት ይገለፃል። በዚህ ማህበር ሥር የሚንቀሳቀሰው የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ዋና ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እና በተለያየ ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን እውነታዎች እንዲታዩ በማድረግ እና ሰብአዊ ክብርን በጠበቀ መልኩ በካቶሊካዊት ቤተክርስትያን አስተምህሮ አማካኝነት የቤተክርስቲያንን እና ህዝባዊ ፖሊሲዎችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት “የእናት ምድር ሴቶች ጠባቂዎች” በሚል ራዕይ በታንዛኒያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በማላዊ ጉልህ እንቅስቃሴ በማድረግ በመላው አፍሪካ ተደራሽነቱን እያስፋፋ እንደሚገኝም ጭምር ተገልጿል።
በድርጊት ማበረታታት
በአፍሪካ የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ኤቭሊን ማሊሳ ንቴንጋ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ በአህጉሪቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ሴቶች ከደረሰባቸው የተለያዩ አእምሮአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዲያገግሙ መርዳት፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማገዝ እና ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተረፉ ሰዎችን መልሶ በማቋቋም ላይ በማተኮር ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ህብረቱ እንደ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ኢስዋቲኒ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጊኒ ኮናክሪ እና በመሳሰሉት ሀገራት ውስጥ እነዚህን ፕሮግራሞች የሚያከናውነው ከዓለም ካቶሊካዊት የሴት ድርጅቶች ማህበር ጋር በመተባበር ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ከካሪታስ፣ ከሀይማኖት ጉባኤዎች እና ከምእመናን ማኅበራት ጋር ያለው ሽርክና ሥራዎቹ የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሏል።
በኬንያ የሚገኘው የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ከሃገሪቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር በንቃት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፥ እንደ ኤልሳቤት የመሳሰሉ ተባባሪ ምዕመን ባለሙያዎች በወላጅነት እና በማህበረሰብ ልማት ላይ ስልጠና እንደሚሰጡ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ህብረቱ በታንዛኒያ እንደ ‘ራይዝ ኤንድ ሬይዝ’ እንዲሁም ‘ሴት ሚ ፍሪ’ ከሚባሉ ተነሳችነቶች ጋር በመሆን በእስር ላይ ለሚገኙ እና ለአደጋ የተጋለጡ ሴቶችን በመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
ስልጠና እና ክልላዊ ወርክሾፖች
ወይዘሮ ኤቭሊን ንቴንጋ የአቅም ግንባታ የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ስትራቴጂካዊ ማዕከል መሆኑን ጠቁመው፥ ህብረቱ በኬንያ ከ25 ሀገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ሴቶች ስልጠና ያገኙበትን ፕሮግራም ጨምሮ ክልላዊ ወርክሾፖችን እና የስልጠና መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በ 2015 ዓ.ም. በታንዛኒያ የተካሄደው ተመሳሳይ አውደ ጥናት ከ21 ሀገራት የተውጣጡ በርካታ ሴቶችን ያሰባሰበ ሲሆን፥ በዩጋንዳም መስከረም 2014 ዓ.ም. አጠቃላይ ስልጠና እንደተዘጋጀ እና እነዚህ አውደ ጥናቶች በፕሮፖዛል አፃፃፍ፣ በገንዘብ ማሰባሰብ፣ በተሟጋችነት እና በማህበራዊ ተግባራት ላይ አተኩረው እንደነበር ገልጸዋል።
የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት የንቅናቄውን ተደራሽነት እና ተሟጋችነት ለማስፋፋት ‘ኢንቪንዝብልስ’ ወይም በአማሪኛ አቻ ትርጉሙ ‘የማይታዩት’ የሚል ዘጋቢ ፊልም እንዳዘጋጀ እና የክልል አምባሳደሮችን እንዳሰለጠነ ተናግረዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሴቶችን ድምጽ ማዳመጥ
ህብረቱ በ 2014 ዓ.ም. በ 42 የአፍሪካ ሀገራት ከ10,000 በላይ ሴቶችን ምስክርነት በማዳመጥ ታሪካዊውን “የአፍሪካ ሴቶች ጩኸት” የሚል ዘመቻ እንዳስጀመረ እና የዚህም ዘመቻ ዋና ዓላማ ከተለያዩ ማህበረሰቦች የተውጣጡ ሴቶችን ተግዳሮቶች፣ ጽናት እና ምኞቶችን ለመረዳት ብሎም ለመመዝገብ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ የዘመቻ እንቅስቃሴ የሚገኙ ግብአቶች የሀገር ውስጥ ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ እና የሃዋሪያዊ ሥራዎቹ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለማሳወቅ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ጭምር ፕረዚዳንቷ አብራርተዋል።
ዘላቂ ጥምረትን መፍጠር
የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት አመራር ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ተባብሮ መስራቱ ዘላቂ የሆነ ተፅእኖ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑን እንደሚገነዘብ የጠቆሙት ወይዘሮ ኤቭሊን ፥ ይህም በመሆኑ ከመንግስት ተቋማት፣ ከህግ አስከባሪዎች እና ከቤተክርስትያን አመራሮች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፥ ህብረቱ እንደ ዋትስ አፕ (WhatsApp) የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በመጠቀም እና ውክልናውን በአፍሪካ አህጉረ ስብከት በማስፋት የዲጂታል መሠረተ ልማቱን እያሳደገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“ይሄንን ብቻችንን ማድረግ አንችልም” ያሉት ፕረዚዳንቷ፥ በሴቶች ሕይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የመንግሥታት፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ስትራቴጂካዊ ሃሳቦች
የዓለም የሴት ታዛቢዎች ህብረት ለቀጣዩ ዓመት ስትራቴጂካዊ ሃሳቦችን ያዘጋጀ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል በአፍሪካ ውስጥ ላሉ ሁሉም የህብረቱ ተወካዮች አህጉራዊ የማስተባበሪያ ስብሰባዎችን ማደራጀት፣ የዲጂታል ስልጠና እና የተወካይ አምባሳደር ትስስሮችን ማስፋፋት፣ የምርጥ ተሞክሮዎች እና ጥናቶች መገልገያ ቤተ-መፃህፍት መፍጠር እና ከሀይማኖት ጉባኤዎች እና ንቅናቄዎች ጋር ያለውን አጋርነት ማጠናከርን የመሳሰሉ ተግባራት ይገኙበታል ተብሏል።
ህብረቱ ከሃምሌ 21-25 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በኡጋንዳ ለሚካሄደው የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ኤቭሊን፥ ሴቶችን እምነትን መሰረት ባደረገ እና ተግባርን ላማከለ አገልግሎት ለማብቃት ያለው ቁርጠኝነት የማይናወጥ ነው ሲሉ ገልጸው፥ በመጨረሻም ህብረቱ በማደግ ላይ ባለው አሻራው እና በእምነት ላይ በተመሰረተ ተልእኮው አማካይነት፥ በአፍሪካ ውስጥ ላሉ ሴቶች የመደመር፣ የሰብዓዊ ክብር እና የለውጥ ወሳኝ ሃይል እየሆነ መጥቷል በማለት አጠቃለዋል።
"ሴቶችን እናክብር፥ ክብራቸውን፣ መሠረታዊ መብቶቻቸውን እናክብር፥ ይሄንን ካላደረግን ማህበረሰባችን እድገት አይኖረውም"
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ