የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት ጋዛ ላይ የተጣለው የዕርዳታ ክልከላ እንዲነሳ ጥሪ አቀረበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በእስራኤል እና በታጣቂው ሃማስ መካከል የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ካበቃ በኋላ፣ እስራኤል ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚገመተው ህዝብ ሁሉንም የምግብ፣ የውሃ እና የመድኃኒት አቅርቦቶች መከልከሏ ለትችት እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች ሲያጋልጣት ሰንብቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ጊዜ ጀምሮ ከ5 ፍልስጤማውያን አንዱ በከፋ ርሃብ ውስጥ እንደሚገኝ በመግለጽ፥ ይህ ማለትም 500 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን በከፋ ርሃብ ውስጥ እና አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሚያመላክት ነው ብሏል።
በእንግሊዝ እና በዌልስ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይፋዊ የእርዳታ ኤጀንሲ የሆነው የካቶሊክ የውጭ ሃገራት የልማት ኤጀንሲ “ካፎድ” (CAFOD) የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተወካይ የሆኑት ኤልዛቤት ፉኔል የእርዳታ እገዳው ማብቃት እንዳለበት ጠቅሰው፥ “ፈጣን፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና እገዳ የማይደረግበት እርዳታ በነፃነት መንቀሳቀስ አለበት” ብለዋል።
ካፎድ (CAFOD) የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ አካል ሲሆን፥ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በላቲን አሜሪካ ካሉ ማህበረሰቦች ጋር ድህነትን፣ ኢፍትሃዊነትን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እና ለሰብአዊ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ብሎም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎችን ለመርዳት በቅርበት በመስራት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።
የማይቀረው ረሃብ ማስጠንቀቂያዎች
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ ተቋም በጋዛ ያለው የድንገተኛ አደጋ ሰብዓዊ ዕርዳታ ሁኔታ በአደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኑን በመጠቆም፥ በአከባቢው ረሃብ መከሰቱ የማይቀር መሆኑን አስጠንቅቋል።
ምንም እንኳን ከባድ ፈተናዎች ቢኖሩም፥ በአከባቢው የሚገኙ የካፎድ አጋር ሰራተኞች እና ድርጅቶች በችግር ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በሚችሉት አቅም በመርዳት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ወይዘሮ ኤልሳቤት የካፎድን መግለጫ አስመልክተው እንደተናገሩት እስራኤል የተጠናከረ የምድር ጥቃት መጀመሯን በማወጅ የተወሰነ የምግብ አቅርቦትን ወደ ጋዛ እንደምትፈቅድ መግለጿን ተከትሎ የተሰጠ መግለጫ መሆኑን አስረድተዋል።
ለተኩስ አቁም ስምምነት እና ያልተገደበ የእርዳታ እንቅስቃሴን አስመልክቶ የተደረጉ ጥሪዎች
“ይህ ቀውስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የካፎድ ፍላጎት አሁንም አልተለወጠም” ያሉት ፉኔል፥ “አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ያልተገደበ ዕርዳታ እንዲደረግ እና ዩናይትድ ኪንግደም ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭን እንድታቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲሉ የድርጅታቸውን አቋም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ኤልሳቤት በማከልም፥ ህዝብን በቦምብ መደብደብ እና ለረሃብ ማጋለጥ እንዲሁም የእርዳታ ተደራሽነቱን መገደብ የዓለም አቀፍ ህግን መጣስ እንደሆነ በመጥቀስ፥ “በሺህ የሚቆጠሩ የእርዳታ መኪኖች እንዳይገቡ ተከልክለው ድንበር ላይ እየጠበቁ ናቸው” ሲሉ በምሬት ከገለጹ በኋላ፥ እገዳው በአስቸኳይ ቆሞ ፈጣን፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተቋረጠ ዕርዳታ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበው፥ “ምንም ይሁን ምን፣ የካፎድ አጋሮች እየተሰቃዩ ያሉትን ለመርዳት በሚያደርጉት ስራ ትልቅ አደጋ እያጋጠማቸው ነው” በማለት ገልጸዋል።
የአጋሮች ደህንነት ስጋት
ለአብነትም ያክል በሳምንቱ መጨረሻ ላይ፣ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ማህበረሰቦች ወሳኝ የጤና አገልግሎት በሚሰጡ በካሪታስ እየሩሳሌም የሚደገፉ ሁለት የህክምና መስጫ ቦታዎች አቅራቢያ የአየር ድብደባዎች እንደደረሱ ገልጸዋል።
ይሄን ተከትሎ የካፎድ መግለጫ እንዳብራራው፣ አጋሮች ለደህንነት ሲባል የእርዳታ ማቅረቢያ ጣቢያዎቻቸውን በፍጥነት እየገመገሙ መሆኑን፥ ነገር ግን ለመርዳት ባላቸው ቁርጠኝነት ጸንተው እንደቀጠሉ አብራርቷል። ተቋሙ ምንም እንኳን በአቅርቦት እጥረት የተነሳ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ቢኖርም አሁንም ድረስ አንዳንድ ምግቦችን እያቀረበ መሆኑን ጭምር ተገልጿል።
'እውነተኛ ረሃብ ነው'
አንዳንዶች ነገሩን ቀለል ለማድረግ በሌላ ስም ሊጠሩት ቢሞክሩም ነገር ግን ይህ እውነተኛው ረሃብ ነው ያሉት የካፎድ አጋሮች፥ “በጋዛ ውስጥ ያለነው ሁላችንም በስተመጨረሻው እንራባለን” በማለት አስጠንቅቀዋል።
በካሪታስ እየሩሳሌም የሚተዳደረው ዋናው የህክምና ማዕከል ቀውሱ በጀመረበት ዓመት ላይ ጥቃት ደርሶበት በደህንነት ስጋት ምክንያት ተዘግቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ምንም እንኳን ከባድ የቦምብ ድብደባ እና ሽባ የሚያደርጉ እገዳዎች ቢኖሩም፣ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ለእናቶች እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘውን ማዕከሉን መልሶ በመገንባት በተሳካ ሁኔታ መክፈት እንደቻለ እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ለመድረስ በጋዛ ዙሪያ እንዲሰማሩ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።