የመጋቢት 07/2017 ዓ.ም ዘመፃጉዕ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ንባባት
1. ገላትያ 5፥1-26
2. ያዕ. 5፥14-20
3. ሐዋ 3፥1-11
4. ዮሐ 5፥ 1-24
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ ዐንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር። በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው።
ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው። ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። 9ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ።
ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።
እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደ ፈወሰው አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።
ወልድ ሕይወትን ይሰጣል
አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ አብ ወልድን ስለሚወድድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
“እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።
የእለቱ የእግዚአብሔር ቃል አስተንትኖ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሁሉ!
ዘወትር የሚወደንና በቃሉ አማካይነት ለሕይወታችንም የሚጠቅመውን እና የሚያሻግረንን ምክር የሚሰጠን እግዚአብሔር አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን። እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር የዐብይ ጾም አራተኛ ሳምንት ዘመፃጉዕ ተብሎ ይጠራል። ይህ እለተ ሰንበት እንደ ቅዱስ ያረድ የዜማ ስያሜ "ዘመፃጉዕ" ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በእዚህ እለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሽተኞችን ስለማዳኑ፣ ታአምራትን ስለማድረጉ፣ ጎባጣዎችን ስለማቅናቱ፣ ለምጻሞችን ስለማንጻቱ፣ ስለ መልኮታዊ ማዳኑ እና ታአምራቱ ይመለካል። "መፃጉዕ" ማለት በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ፣ የተያዘ በሽተኛ ማለት ሲሆን ቅዱስ ያሬድ በክርስቶስ ስለተፈወሱ ሰዎችና ስለክርስቶስ ፈዋሽነት የዘመረው የመዝሙሩ መክፈቻና ርዕስ በመሆኑ እለቱ "መፃጉዕ" ተብሎ ተጠርቷል።
በዚህ ዕለተ ሰንበት በተለይም በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር ቃል ሊያስተምረን፣ የሕይወትን መንገድ ሊያመላክተን በተነበቡት ንባባት አማካኝነት የእያንዳንዳችንን ልብ በር ያንኳኳል።
የዐብይ ጾም ወቅት ጌታን ለእያንዳንዳችን እና ለመላው ቤተ ክርስቲያን ወደ ኢየሱስ ምሕረት መለወጥ እንድንችል ጸጋን የምንጠይቅበት ጊዜ ነው። በእውነቱ በጣም ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች በህይወት እና በስህተታቸው ሲዳከሙ ወደ ፊት በድጋሚ ተነስተው ለመገስገስ የሚረዳቸውን መንፈስ ቅዱስ ከመማጸን ይልቅ የልቦቻቸውን በሮች መዝጋት የተካኑ ናቸው።
የእግዚአብሔር ቃል "የፈውስ ውኃ" በማለት ሕዝቅኤል (47፣1-9.12) ከመቅደሱ ስለሚፈሰው ውኃ ሲናገር "የተባረከ ውኃ የእግዚአብሔርም ውኃ እንደ እግዚአብሔር ቸርነት የበዛ ሁልጊዜም ብዙ" ነው ይላል። ጌታ እንዲያውም “ፍቅሩን በመስጠት፣ ቁስላችንን በመፈወስ” ለጋስ እንደሆነ ገልጿል።
ውሃ በዮሐንስ ወንጌል (5፡1-25) ተመልሶ የመጠመቂያ ሥፍራ እንደ ሆነ በመግለጽ "በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ተብሎ በሚጠራበት ሥፍራ የነበረ፣ አምስት መግቢያዎች ያሉት ሥፍራ ሲሆን በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር የሚል ወግ ነበረ።
"በዚህ ሥፍራ ብዙ ሰዎች ነበሩ" ይላል የዛሬው ቅዱስ ወንጌል። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ “ተስፋ ያጣ” “የተሸነፈ ሰው” ገጥሞታል። ሰውዬው ታሟል፣ ነገር ግን ሊሰመርበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ይህ ሰው የታመመ እና ተስፋ የቆረጠ "ሽባ የሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በእውነቱ ሌላ በጣም መጥፎ በሆነ በሽታ ተይዟል፣ በስንፍና በሽታ በጣም ታሞ ነበር።
እንዲያዝን ያደርገው እና በተጨማሪም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳይፈወስ ያደረገው ስንፍና ራሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በኢያሪኮ ይኖር የነበረውን ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ማስታወስ ተገቢ ነው። እርሱም “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ ጮኸ። ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ አብዝቶ ጮኸ። ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እንደገና ማየት እንድችል አድርገኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እይ! እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም እያወደሰ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ (ሉቃስ 18፡35-43)። በዛሬ ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ሰው ግን ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በሕመም ሲሰቃይ ቢቆይም ቅሉ ነገር ግን ከበሽታው ለማገገም አልፈለገም፣ ምንም ጥንካሬ አልነበረውም። በተመሳሳይ ጊዜ “በነፍሱ ውስጥ መራራ ስሜት ነበረ፣ በጣም ያጉረመርም ነበረ፣ ‘ሌላው ግን ቀድሞኝ ደርሶ እኔ ወደ ጎን ቀርቻለሁ" እያለ የምያጉረመርም እና በጣም የምያማርር ሰው ነበረ። በተጨማሪም በሌሎች ላይ ቂም ይዞ ነበረ። እርሱ "በእውነት አሳዛኝ ነፍስ የነበረው፣ በህይወት የተሸነፈ" ሰውነበር።
“ኢየሱስም አዘነለት” እና “ተነስ!" እኔ ይህ ታሪክህ ማብቂያ እንዲያገኝ አደርጋለሁ ብሎት ከተኛበት አስነሳው። እርሱም አልጋውን ይዞ ተነሳ። አልጋህን ይዘህ ሂድ አለው። ከዚያም ሌላ ትይንት እናያለን። “ወዲያው ያ ሰው ተፈውሶ አልጋውን አንስቶ መራመድ ጀመረ፣ ለብዙ አመታት ያህል በጣም ታምሞ ስለነበር ማመን አቃተው ምናልባትም ትንሽ ተጠራጣሪ የነበረ ሰው በመሆኑ የተነሳ በድንገት በመንገድ ላይ ልታመም እችላለሁ ብሎ በመስጋት አልጋውን በትክሻው ላይ ተሸክሞ ሄድ። በዚህ ጊዜ ሌሎች ገፀ-ባህሪያት ወደ ታሪኩ ይገሉ፡- “ቀኑ ቅዳሜ ነበር፣ እናም ያ ሰው ምን ገጠመው? የሕግ መምህራን ያገኙታል፣ ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው፥ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው ‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ አለኝ፤” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም “‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም የፈወሰኝ ሰው ማን መሆኑን አልውቅም በማለት መለሰ።
ከዚያም አንድ እንግዳ ነገር ተከሰተ "እነዚህ ሰዎች 'ከመደሰት እና "እንዴት ቆንጆ ነገር ነው የተደረገልህ! እንኳን ደስ ያለህ!' ከማለት ይልቅ አይሁዳዊያኑ በድርጊቱ በሽቀው ስለጉዳዩ ምርመራ ማድረግ ይጀምራሉ፣ እዚህ ላይ ምን እንደተፈጠረ እንይ፣ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን ህግን መጠበቅ እና ማክበር አለብን። ሰውዬው በበኩሉ አልጋውን ተሸክሞ መጓዙን ቀጥሏል፣ ግን ትንሽ አዝኗል። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለው ሰው አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ምንባብ በመቀጠል ኢየሱስ “ይህን ሰው ዳግመኛ አግኝቶ እንዲህ አለው:- “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፣ ነገር ግን ወደ ኋላ አትመለስ ማለትም፣ ደግመህ ኃጢአት አትሥራ፤ ይህም የከፋ ነገር እንዳይደርስብህ ነው። ወደ ፊት ቀጥል፣ ወደፊት መጓዝህን ቀጥል ይለዋል። እናም ያ ሰው “የፈወሰኝ ሰው ኢየሱስ ይባላል” ብሎ ወደ ህግ መምህራን ዘንድ ሄዶ ያቃጥራል ወይም ይነግራቸዋል።
ስለዚህም አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ በሰንበት ይህን አድርጎ ነበርና። ምክንያቱም በሰንበት ምንም መልካም ነገር እንኳን ማድረግ አለተፈቀደለትም። ይህ ታሪክ በእኛም ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ ይከሰታል። በነፍሳችም ውስጥ ሕመም ሊገጥመን ይችላል፣ በሕይወት ውስጥ ብዙ ስህተቶችን አድርገን ይሆናል፣ በተወሰነ ቅጽበት ውስጥ እንደ ውኃ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች በውስጣችን እንዳሉ ሆነው ይሰማናል፣ ወይም አንድ ቃል ይሰማናል። እናም እሱ ምላሽ ይሰጣል። መሄድ ትፈላጋለህን? ብሎ ይጠይቀናል፣ ስለዚህ "አይዞህ ተነስ እና ሂድ ይለናል። ነገር ግን ዛሬ በክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ ብዙ ጊዜ በሮች ተዘግተው ይገኛሉ። ምናልባት ሰዎች “አትችልም፣ አይሆንም፣ አትችልም” ሲሉ ሰምተህ ይሆናል። እዚህ ስህተት ሰርተሃልና አትችልም ይሉናል። መምጣት ከፈለጋችሁ እሁድ ወደ ቅዳሴ ኑ፣ ነገር ግን እዚያ ቆዩ፣ ነገር ግን ብዙ አታድርጉ እያለን መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሕግ ዶክተሮች ሥነ ልቦና ያላቸው ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ሲያስቆሙ እንመለከታለን።
እንደዚህ ማድረግ ግን አይገባንም፣ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ቤት ናት፣ ኢየሱስም እኛን ይቀበላል፣ ነገር ግን መቀበል ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ለማግኘት ይወጣል ይሄዳል። ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ ምንም ጊዜና ቀን ሳይገድበው ወደ እኛ ይመጣል። እና ከተጎዱ ሰዎች ጋር ይራመዳል፣ ይሸከማቸዋል፣ ይህ ደግሞ "ምህረት ይባላል" አምላክ “ሕዝቡን:- መሥዋዕትን ሳይሆን ምሕረትን እሻለሁ" ሲል ሲገሥጽ የተናገረው ይህንኑ ነው።
አሁን በዐብይ ጾም ወቅት ላይ እንገኛለን፣ መለወጥ አለብን። አንድ ሰው እንዲህ አለ፡ - "አባ በመንገድ ላይ ብዙ ኃጢአተኞች አሉ: የሚሰርቁ፣ ሰውን የሚንቅፉ፣ የሚሳደቡ .... ወዘተ" ብሎ ይናገራል። እንዲ እያልን እነዚህን ሰዎች እንንቃቸዋለን። ነገር ግን ለዚህ ሰው እንዲህ ማለት አለብን "እና አንተ? ማነህ፧ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ስላነሣሣው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመቀላቀል ሲመጣ የልብህን ደጅ የምትዘጋው አንተ ማን ነህ? ዛሬም ቢሆን “ይህ ኑፋቄ ነው፣ ይህ ማድረግ አይቻልም፣ ይህ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚጻረር ነው፣ ይህ ከሕግ ጋር የሚጋጭ ነው” በማለት የሚቃወሙ እና የሕግ መምህራን የሚመስሉ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ላይ ያደረጉትን ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ ክርስቲያኖች አሉ። እናም ስለዚህ ለብዙ ሰዎች በሮችን ይዘጋሉ። ስለዚህም ወደ ኢየሱስ ምሕረት እንድንለወጥ ዛሬ ጌታን እንለምነው፣ በዚህ መንገድ ብቻ ሕጉ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። ምክንያቱም ሕጉ እግዚአብሔርን እና ባልንጀራዎቻችንን እንደ ራሳችን መውደድ እንዳለብን ያስተምረናልና!
ይህንን ለማድረግ የእናታችን ቅድስት ድንግል ምርያም አማልጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!