ፈልግ

Cookie Policy
The portal Vatican News uses technical or similar cookies to make navigation easier and guarantee the use of the services. Furthermore, technical and analysis cookies from third parties may be used. If you want to know more click here. By closing this banner you consent to the use of cookies.
I AGREE
የማታ ጸሎት በላቲን ቋንቋ
መርዐ-ግብር በድምጽ የቀረበ ዘገባ
የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ የካቶሊክ እህቶች ‘በይቅርታ ውስጥ የተለያየ ጸጋን እናገኛለን’ አሉ የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ የካቶሊክ እህቶች ‘በይቅርታ ውስጥ የተለያየ ጸጋን እናገኛለን’ አሉ  

የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ የካቶሊክ እህቶች ‘በይቅርታ ውስጥ የተለያየ ጸጋን እናገኛለን’ አሉ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ግንባር ቀደም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፀረ-የሞት ቅጣት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ‘ካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ኔትወርክ’ በተለይ በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮግዛት ውስጥ በርካታ ሥራ እየሰሩ የሚገኙትን የኦርሶላይን እህቶች ታሪክን አካፍሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በየ 25 ዓመቱ ተመራጩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ እርቅን፣ መለወጥ እና ነጻ መውጣትን ለመሻት ልዩ የሆነ የኢዮቤልዩ ዓመትን የሚያውጁ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዘንድሮው የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ቃል በኩል ግጭት፣ ፍርሃትና ጥርጣሬ በጣም የተለመደ በሆነበት ዓለም ውስጥ “ተስፋ መቁረጥ” እንደማይገባን አስታውሰውናል።

ቅዱስ አባታችን ይሄን አስመልክተው እንዳብራሩት፣ “በዓለማችን ላይ ያለውን ታላቅ መልካምነት ልንገነዘብ ይገባናል፥ እራሳችንን በክፋትና በዓመፅ እንደተሸነፍን አድርገን ማሰብ ዬለብንም” ብለዋል።

በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ለሁላችን ብርታትን እና ተስፋ ሊሰጡን ከሚችሉ እንዲሁም ይህንን አስደናቂ ምስክርነት በተግባር ካሳዩ በክሊቭላንድ ኦሃዮ ግዛት ከሚገኙ የኦርሶላይን ገዳማዊያት የሴቶች ቡድን ጋር በቅርበት የመሥራት እድልን ያገኙት የካቶሊክ ሞብላይዚንግ ኔትዎርክ አባል የሆኑት ሲስተር ክሪሳኔ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እ.አ.አ. በ 1995 ዓ.ም. በክሊቭላንድ ግዛት የኦርሶላይን ገዳም አባል የሆኑት ሲስተር ጆአን ማሪ ማስቻ ከጉባኤው መኖሪያ ቤት ጀርባ በሚገኝ ስፍራ ዳንኤል ፒቸር በተባለ ሰው በተደፈሩበት እና በተገደሉበት ወቅት የገዳሙ ማህበረሰብ ክፉኛ አዝኖ እንደነበር ያነሱት ሲስተር ክሪሳኔ፥ እህት ጆአን ማሪ የማህበረሰባቸው ተወዳጅ አባል የነበሩ ሲሆን፥ የዋህ ነፍስ ያላት እና በዓለም ላይ ሰላም እና ፍትህን ለማምጣት በመሥራት የምትታወቅ እህት ነበረች ብለዋል።

ከግድያው በኋላ የኦርሶላይን እህቶች የግድያውን ወንጀል የፈጸመው ፒቸር የሞት ፍርድ ሲፈረድበት ተቃውሞዋቸውን አሰምተው የነበረ ሲሆን፥ አቃቤ ህጎቹ ይህንን የገዳማዊያኑን ፍላጎት ችላ በማለታቸው በዓለም ዙሪያ ካሉ እህቶች አቃቤያኑ የሞት ቅጣትን እንዲያስቀሩ በሚማጸኑ መልዕክቶች እና የስልክ ጥሪዎች ተጨናንቀው እንደነበር አስታውሰዋል።

ወንጀለኛው ላጠፋው ጥፋት የሞት ቅጣት እንዳይፈረድበትም ገዳማዊያቱ አጥብቀው ሲጸልዩ እንደነበር ያስታወሱት እህት ክሪሳኔ፥ በመጨረሻም ፒቸር የሞት ቅጣቱ ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም ዳኛው ግን የሞት ቅጣቱን እንደሻሩት ገልጸዋል።

ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ በቅርቡ ገዳማዊያኑ ከፒቸር ደብዳቤ የደረሳቸው ሲሆን፥ በደብዳቤው በድሪጊቱ መጸጸቱን እና ማዘኑን በመግለጽ ገዳማዊያቱን ይቅርታ ጠይቋል። በእህት ጆአን ማሪ ግድያ የተጎዱ የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በውሳኔያቸው መስማማታቸውን የማረጋገጥ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ገዳማዊያቱ ለፒቸር ደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህም ደብዳቤያቸው ይቅርታውን የተቀበሉ ሲሆን፥ ፒቸር በፈጸመው ወንጀል ካስከተለባቸው ስቃይ እና ህመም ማምለጥ እንዳልቻሉ በግልጽ በመንገር “ህይወቷን ስታጠፋ ማህበረሰባችንን፣ ቤተሰቧን እና ወዳጆቿን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማስፋፋት ብቻ የሚፈልግ የዋህ ሰው አሳጣህ” በማለት ከገለጹለት በኋላ፥ ሆኖም ግን በቀሪው ዘመኑ “ደግ፣ ሰላማዊ እና መልካም ሰው” እንዲሆን አበረታተው ይቅርታውን ተቀብለው እነርሱም ይቅርታ ጠይቀውታል።

ይህ የደብዳቤ ልውውጥ እና በማህበረሰባቸው ውስጥ ያለው ጥልቅ ልምድ ገዳማዊያቱ በኦሃዮ ግዛት የሞት ቅጣትን ለማስቆም እያደረጉት ያለውን ጥረታቸውን እንዲያድሱ አነሳስቷቸዋል ያሉት እህት ክሪሳኔ፥ ፒቸር የሞት ቅጣቱ ተፈጽሞበት ቢሆን ኖሮ፣ ይህ የደብዳቤ ልውውጥ ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል ገልጸው በዚህም ገዳማዊያቱ የይቅርታ እና የእርቅ በሮች ለሌሎች ዝግ እንዳይሆኑ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ ብለዋል።

ይህ የኦርሶላይን እህቶች ጠንካራ ታሪክ ስለ ይቅርታ የሚነገሩ አንዳንድ አላስፈላጊ ትርክቶችን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፥ ከዚህም በላይ ሌሎች ለእንደዚህ አይነት ለውጦች እና ፈውስ ክፍት እንዲሆኑ ይጋብዛል ብለዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ይቅርታ ማለት የተደረገውን ወይም የደረሰውን ጉዳት መርሳት ማለት እንዳልሆነ፥ ይሄንንም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው በሆነው ፍራቴሊ ቱቲ (252) ላይ “የበቀል አዙሪት ወይም የመርሳት ግፍ ውስጥ ሳንወድቅ ፍትህን እንድንከተል የሚያስችለን ከልብ ይቅር ማለት ነው” በማለት ገልጸውታል።

ገዳማዊያቱ በሲስተር ጆአን ማሪ መገደል እና ከማህበረሰባቸው መለየት ያስከተለውን ጉዳት እንዳላስረሳቸው፥ እንዲያውም አንዳንድ እህቶች ውድ ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው በጣም አዝነው እንደነበር፥ ሆኖም ግን ደብዳቤው ሁሉም ይህን ከባድ ሃዘን እንደገና እንዲመረምሩ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።

ሲስተር ላውራ ብሬጋር የተባሉት የማህበሩ አባል እንደተናገሩት “ከፒቸር የተላከውን ደብዳቤ ስከፍት አንድ ቶን የሚያክል ጡብ አናቴን እንደመታኝ ተሰምቶኝ ነበር” ያሉ ሲሆን፥ የተፈጸመውን ግፍ መቼም ቢሆን እንደማይረሱት፥ ሆኖም ግን ይቅር በማለት የጥላቻ እና የጥቃት አዙሪት እንዳይፈጠር ለመከላከል መምረጣቸውን ይናገራሉ።

ይህ ሁኔታ ‘ይቅርታ ማድረግ እና ፍትህ የማይጣጣሙ አይደሉም’ ከሚለው አስተምህሮ ጋር ይገናኛል ያሉ ሲሆን፥ በእርግጥ ገዳማዊያቱን በመጀመሪያ የሞት ፍርድን እንዲቃወሙ እንዲሁም ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ፒቸርን ይቅር ለማለት ያነሳሳው እና ያበረታታው የምህረት ፍቅር ፍትሕን ወደ ተራ የበቀል ፍላጎት በመቀየር ከማዛባት ይልቅ እውነተኛ የፍትህ ራዕይን በማሳደግ የተሻለ ዓለምን ገንብቷል ያሉት ሲስተር ክሪሳኔ፥ በሰው ልጅ ክብር ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን ሳናደርስ ጉዳትን መፍታት እንችላለን ወይም አለብን ብለዋል።

በመጨረሻም እነዚህ ጀግና የሆኑ እህቶች ይቅር ባይነት ደካማ እንዳልሆነ ያሳዩን ሲሆን፥ ድፍረታቸው ጎልቶ የሚታይ ነው። ከዚህም በላይ የእምነታቸው እና የማህበረሰባቸውን ጥንካሬ የሚያሳይ ምስክር ነው። ገዳማዊያቱ የሚያምኑበት መርሆዎቻቸው ለፈተና ሲዳረጉ፣ ከእነዚህ መርሆዎች ጎን መቆም ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል የእነዚያን መርሆዎች እውነተኛ ኃይል አሳይተዋል ብለዋል።

የኦርሶላይን እህቶች የሞት ቅጣትን አንቀበልም ሲሉ፥ ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ እያሳዩ ነው ያሉት ሲስተር ክሪሳኔ፥ በዚህም ውጤት ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ ፒቸር እና መሰሎቹ ፈውስ እና ይቅርታን በመሻት ምላሽ ሰጥተዋል ብለዋል።

ሲስተር ሱዛን ዱርኪን የተባሉ ሌላኛዋ የተቋሙ አባል በበኩላቸው ከፒቸር ጋር የነበረውን የደብዳቤ ልውውጥን በተመለከተ የተደረገውን ስብሰባ ሲገልጹ፣ “በግሌ ምንም ልረዳው ያልቻልኩት በውስጤ የጋለ ልባዊ ስሜት ወይም ተጭኖኝ የነበረ የሆነ ነገር ከላዬ ላይ ሲወርድ ተሰምቶኝ ነበር” ካሉ በኋላ ተስፋ እና ምህረት ለሚመለከታቸው እና ለሰፊው ማህበረሰብ አዲስ የፈውስ መንገዶችን ይከፍታሉ በማለት ገልጸዋል።

በእንደዚህ ያሉ በተስፋ የተሞሉ ታሪኮች በመበረታታት ይቅር ማለት የሚያስገኘውን ያልተጠበቀ ጸጋ መመስከር እንችላለን በማለትም አክለዋል።

ሲስተር ክሪሳኔ በመጨረሻም በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ፈውስን እና ተሃድሶን እንዴት በምህረት እና በተስፋ ልናገኝ እንደምንችል አጥብቀን በምናሰላስልበት በአሁኑ ወቅት፥ የኦርሶላይን እህቶች መንገዱን በእውነት እንዳሳዩን በመግለጽ፥ ከእነሱ ጋር በመሆንና የአምላክን መንግሥት በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ላይ ለመገንባት ጠንክረን በመሥራት ለሚሰጡት ምሥክርነት ምላሽ እንስጥ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 

11 Mar 2025, 13:22
Prev
March 2025
SuMoTuWeThFrSa
      1
2345678
9101112131415
16171819202122
23242526272829
3031     
Next
April 2025
SuMoTuWeThFrSa
  12345
6789101112
13141516171819
20212223242526
27282930