ብፁዕ ካርዲናል ሆለሪች የሰላም ሥነ ምግባርን ወደ ነበረበት መመለስ ይገባል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሉክሰምበርግ ሊቀ ጳጳስ እና የብጹአን ካርዲናሎች ምክር ቤት አባል ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት በመሆን ለዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን የአውሮፓ የፖለቲካ እንቅስቃሴን የሚከታተሉ ናቸው።
ብጹእ ካርዲናሉ በቅርብ ቀናት በአውሮፓ መሪዎች የጸደቀውን 'Rearm Europe' ተብሎ የተጠራውን አውሮፓን መልሶ የማስታጠቅ ፕሮግራም ላይ ያላቸው ግምገማ ምን እንደሚመስል ተጠይቀው፥ “በመጀመሪያ መናገር ያለብኝ ይህ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ተጠናክሮ የቀጠለው የጦር መሳሪያ ውድድር በጣም አሳሳቢ እና አደገኛ እየሆነ መጥቷል” ካሉ በኋላ፥ ማንኛውንም የፖለቲካ ሀሳብ ከማቅረባቸው በፊት የአብዛኛውን የዓለም መሪዎች ላይ የሚታየውን የሞራል ግንዛቤ ማሽቆልቆሉን ማሰላሰል እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ጦርነትን አጥብቆ መቃወም አሁን ላይ ጨርሶውኑ የጠፋ እንደሚመስል ጠቁመው፥ ያንን የሞራል ግንዛቤ መልሶ ማምጣት ካልተቻለ በስተቀር የትኛውም የፖለቲካ ስልት ውጤታማ እንደማይሆን ብሎም ዓለም በአደገኛ ጎዳና ላይ የመጓዝ አደጋ ተጋርጦባታል ብለዋል።
ይህ በእርግጠኝነት የሞራል ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ካርዲናሉ፥ ነገር ግን ጉልህ በሆኑ የፖለቲካ ለውጦች የተሸፈነ ሊመስል እንደሚችል ገልጸው፥ ከእነዚህ ለውጦች ውስጥ በጣም ጉልህ የሆነው የባለብዙ ወገንነትን ወይም መድብለ መንግስትነትን የመተው ዝንባሌ እንደሆነ እና ዛሬ ላይ በግልጽ የሚታየው የኃያላን መንግሥታት የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጥቅሞች የማስቀደም አሮጌ ጽንሰ-ሐሳብ መስፋፋትት እንደሆነ በመጥቀስ፥ ነገር ግን ዓለም ሰላምን መልሶ ማግኘት የሚችለው በባለብዙ ወገን ማዕቀፍ ውስጥ ሲካተት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛ የሆነ የመድብለ መንግስት አስፈላጊነትን እና ይህም አካሄድ የዲፕሎማሲው የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ አጥብቀው ይናገሩ እንደነበር ገልጸው፥ እሳቸውም በዚህ ሃሳብ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አውሮፓም 800 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ፕሮግራም በማዘጋጀት ላይ እንደሆነች እና አህጉሪቷ እውነተኛ ስትራቴጂካዊ ስጋቶች አሉባት ወይ ተብለው የተጠየቁት ብጹእ ካርዲናል ዣን ክላውድ፥ “በአንዳንድ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ወይም አባልነት በሚፈልጉ ሃገራት ላይ ተጨባጭ የአደጋ ስሜት እና አሳሳቢነት መኖሩን አስታውሰው፥ “እኔ እንደማስበው ሩሲያ እና ሞልዶቫን የሚያዋስኑት የባልቲክ ግዛቶች ላይ ቀጣይነት ያለው አለመግባባት ያመጣሉ” ብለዋል።
ቀስ በቀስ እየታወጀ ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ከእነዚህ አከባቢዎች ለቆ የመውጣት ዜና እነዚህን ሀገራት እንደሚያሳስባቸው የጠቆሙት ካርዲናሉ፥ በዚህም የተነሳ የአውሮፓ ህብረትን በመከላከል ላይ የተመሰረተ ወታደራዊ አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ “የአውሮፓ ኅብረት የተወለደው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አመድ ላይ እንደመሆኑ መሰረታዊ መርሆው ሰላም ነው” በማለት ሰላም የህልውናዋ ምክንያት እንደሆነ ካስታወሱ በኋላ፥ ህብረቱ የተፈጠረው በአውሮፓ መንግስታት ወይም በአውሮፓ ውስጥ ጦርነቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገው የፖሊሲ ለውጥ በአውሮፓ ላይ እየታየ ያለውን የመከላከያ አሰላለፍ ላይ ተጽዕኖ ይኖረው እንደሆን የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ ለአውሮፓ መድብለ መንግስትነት ወይም መልቲ-ላተራሊዝም ወሳኙ እና የጋራ የፖለቲካ ምርጫ እንደሆነ በማንሳት፥ “በአትላንቲክ ውቅያኖስ ሃገራት በኩል ይህ አመለካከት እየደበዘዘ ያለ ይመስላል” ካሉ በኋላ፥ አውሮፓ እራሷን ችላ የመከላከል አቅምን ከማዳበር በተጨማሪ በመጠኑም ቢሆን ጠንካራ የፖለቲካ ማንነት መልሳ ማግኘት የምትችል ከሆነ፣ የባለብዙ ወገን ሚናን በማጠናከር እራሷን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚያገለግል እንደሆነ ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ ሆና ስለምትቀጥል አውሮፓ በወታደራዊ ምርት ላይ የበለጠ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥረት ማድረግ አለባት ብዬ አምናለሁ ብለዋል።
ተቺዎች እንደሚሉት በአውሮፓ የጤና፣ የትምህርት እና የማህበራዊ ደህንነት ችግር ውስጥ እንዳሉ ይከራከራሉ፥ ነገር ግን 800 ቢሊዮን ዩሮ ለጦር መሳሪያ እየዋለ ነው፥ የአውሮፓ ማኅበራዊ ደኅንነት ሥርዓት ችግር ውስጥ እያለ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ወታደራዊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚያስደንቅ እንደሆነ ተጠይቀው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጣም ምክንያታዊ የሆነውን መፍትሔ እንዳቀረቡ አምናለሁ” ያሉት ብጹእ ካርዲናሉ፥ ከአውሮፓውያን የጦር መሳሪያዎች ምርት የሚገኘው አጠቃላይ ትርፍ ለማህበራዊ ተነሳሽነቶች በአስገዳጅ ሁኔታ መስጠት እንደሚገባ አሳስበው፥ ማንም ሰው ከጦር መሣሪያ ትርፍ ማግኘት እንደሌለበት እና ይልቁንም እነዚህ ትርፎች ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው በማስታወስ፥ ይህ ወዲያውኑ ሊተገበር የሚችል ሀሳብ እንደሆነ እና በመጪዎቹ ቀናት በቅድስት መንበር የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጋር ሲገናኙ ይሄንን ሃሳብ እንደሚያነሱላቸው ገልጸዋል።