ፈልግ

በስኮላስ ኦኩረንቴስ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ተገናኝተው ሰላም ሲባባሉ በስኮላስ ኦኩረንቴስ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ተገናኝተው ሰላም ሲባባሉ  (Vatican Media)

የእስራኤል፣ የፍልስጤም እና የአሜሪካ ወጣቶች ለሰላም ህብረት መፍጠራቸው ተነገረ

ጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሆነው ‘ስኮላስ ኦኩሬንቴስ’ (Scholas Occurrentes) ‘እውነታዎች ያግባቡናል’ በሚል ጭብጥ በተዘጋጀው ስብሰባ የተሳተፉት ወጣት ተሳታፊዎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ረቡዕ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀረበው ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መጨረሻ ላይ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፥ በሁሉም ተሳታፊዎች የተፈረመ እና ለውይይት ያላቸውን ቁርጠኝነት በሚያመለክተው ደብዳቤ ላይ “እርስ በርስ የመግባባት ችሎታን እንጂ ስምምነትን እየፈለግን አይደለም” የሚል መልዕክት ማስፈራቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“እኔ እስከማስታውሰው ድረስ እርስ በርስ እንዳንነጋገር ተደርጎ ነበር፥ ሌላውን ወገን የማዋረድ ከፍተኛ ዝንባሌ አለ፥ የተለያዩ ትርክቶችን ማውራት እና ማዳመጥን መማር ወሳኝ ነው” ስትል ከእስራኤል የመጣችው አቢግያ ስዞር የሙስሊም፣ የአይሁድ እና የክርስቲያን ወጣቶችን በአንድነት ለሃይማኖታዊ እና ለባህላዊ ውይይቶች አንድ ላይ ባሰባሰበው ‘እውነታዎች ያግባቡናል’ በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ልምዷን በማካፈል፣ ሰላምን ለማስፈን ከሌሎች ጋር መገናኘት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ገልፃለች።

‘እውነታዎች ያግባቡናል’ በሚል መሪ ቃል ከጥር 25 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በቫቲካን የተካሄደው ይህ የውይይት መድረክ የተዘጋጀው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ ያደርሰውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ለውይይት እንዲሁም ለጋራ መግባባት እና ግንዛቤ አስፈላጊነት ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱን በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት በኢየሩሳሌም የዕብራይስጥ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንደገለጹት ውይይቱ ከተለያዩ አስተዳደግ በመጡ ወጣቶች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ የስኮላስ ኦኩሬንቴስ ማህበር ደግሞ ‘እውነታዎች ያግባቡናል’ የተባለውን ዝግጅት በማስተባበር እና የደረሱበትን መደምደሚያ ረቡዕ ዕለት በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከቀረበው ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መጨረሻ ላይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ማቅረባቸው ተነግሯል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ብጹእነታቸው ፊርማቸውን ያኖሩበት ደብዳቤ እና የሹራብ ስጦታ የሰጧቸው ሲሆን፣ በመልዕክታቸውም ያካሄዷቸውን አስቸጋሪ ውይይቶች ላይ ማብራሪያ በመስጠት ግባቸው ስምምነት ሳይሆን የጋራ መግባባት ላይ ለመደረስ መሆኑን አስረድተዋል።

መከፋፈልን ማሸነፍ
በዚህ ልዩ ቦታ ላይ የእስራኤል፣ የፍልስጤም እና የአሜሪካ ወጣቶች ይህን ውስብስብ የሆነ ውይይትን ለማስቀጠል እና የእርስ በርስ አመለካከቶችን ለመረዳት ከፋፋይ ንግግሮችን ወደ ጎን በመተው እና የጥላቻ ንግግርን በመቃወም ወደ ፊት መጓዝ እንደሚገባ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

በቲሸርቷ ላይ በተሰፋ መለያ ላይ የተጻፈውን በጋዛ የተገደሉትን ሰዎች ብዛት የሚያሳይ ቁጥር በመጠቆም “እኔ የመጣሁት እነዚህ ቁጥሮች እንዲቆሙ ስለምፈልግ ነው” በማለት የተናገረችው አቢግያ፥ “ጦርነቱ እንዲቀጥል ወይም ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ እንዲሞቱ አልፈልግም። በጋዛ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዲኖር አልፈልግም። በሁለቱም ወገን በኩል የምወዳቸው እና ለእኔ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጓደኞች አሉኝ” ስትል አክላለች።

በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የመገናኘት እድል ማግኘት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለጸችው የኖትር ዴም ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ኢዛቤል ጎንዛሌስ በበኩሏ ወደ ቤቷ ተመልሳ ለዕርቅ ጥረት አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን የሰማቻቸውን ታሪኮችን፣ ያገኘችውን ልምድ እና የቀሰመችውን ትምህርት ለማካፈል ተስፋ እንዳደረገች በመግለጽ፥ “ሁላችንም በሰላም መኖር እና ደስተኛ መሆን እንፈልጋለን” በማለት ተናግራለች።

ማይሳን ማዲ የተባለችው ፍልስጤማዊው አረብ ውይይቱ ጥልቅ እና ስሜት የሚነካ እንደሆነ በመግለጽ “እኔ ክርስቲያን አይደለሁም፣ ነገር ግን አሁንም የቦታው ቅድስና እና ታላቅነት ይሰማኛል፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቃላት በማይታመን ሁኔታ ኃይለኛ ነበሩ። መሰረታቸው ወይም እምነታቸው ምንም ይሁን ምን እኔ እንደማስበው እዚህ የተገኙት ሁሉም ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቷቸው ነበር” ስትል አረጋግጣለች።

ስነ ጥበብን ከውይይት ጋር የማዋሃድ ትምህርታዊ አቀራረብን የሚከተለው ጳጳሳዊው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነው ስኮላስ ተሳታፊዎቹ በእውነታዎቻቸው ላይ በማሰላሰል ጥበባዊ አገላለጾችን እንደሚጠቀሙ፣ የግል አመለካከቶቻቸውን ውብ በሆነ አቀራረብ ለመግለጽ እና አዲስ የጋራ አስተሳሰቦችን ለመገንባት እንዲችሉ እድል እንደሰጣቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ተሳታፊዎቹ በዘላለማዊዋ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተደረገ “ጥበባዊ የእግር ጉዞ” ተሳትፈዋል።

ስኮላስ ኦኩረንቴስ እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት
ስኮላስ ኦኩረንቴስ በ1993 ዓ.ም. በአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ ከተማ በጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ ማለትም ያሁኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፥ የተቋሙ ዋና አላማ ወጣቶች በማህበረሰባቸው ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንዲለዩ እና እንዲፈቱ ለማስተማር እንደሆነ እና ተልእኮውም ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ወጣቶችን ማለትም ካቶሊኮችን፣ አይሁዶችን እና ሙስሊሞችን በውይይት እና በባህላዊ ትስስር ውስጥ ለማሰባሰብ እንደሆነ ይታወቃል።

ከ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ስኮላስ ስድስት ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ውይይቶችን በማዘጋጀት የጋራ መግባባትን እና ሰላምን በማጎልበት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

ይህ ጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያላሰለሰ ድጋፍ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ወጣቶችን እርስ በርስ በሚያገናኙ ጥበባዊ እና ትምህርታዊ ፕሮጄክቶች ተጽዕኖውን በማስፋፋት በሃይማኖታዊ ውይይት ዓለም አቀፍ መሪ ሆኗል።

በ 2015 ዓ.ም. በሊዝበን ከተማ ከተለያዩ ሃይማኖቶች እና ባህሎች የተውጣጡ ወጣቶችን አንድ ላይ ያሰባሰበው የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ አራት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እና ‘ስድስተኛው የወጣቶች ጸሎት ቤት’ ተብሎ የተሰየመውን የግድግዳ ሥዕል ሰርቶ ዝግጅቱ ላይ በማቅረብ ይታወሳል።

በ 2016 ዓ.ም. ደግሞ ተቋሙ ተልዕኮውን ወደ ኢንዶኔዥያ በማስፋት ከ1,000 በላይ የሚሆኑ የካቶሊክ እና የሙስሊም ወጣቶችን በጋራ በማሰባሰብ እጅግ ግዙፍ የሆነ እና በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል ያለውን ተስማምቶ የመኖር ተምሳሌትነትን የሚገልጽ ሃውልት በመስራት ይታወቃል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሚደገፉት እነዚህ ውጥኖች ጥበብ፣ ትምህርት እና በሃይማኖቶች መካከል ለውይይት ያለው ቁርጠኝነት ልዩነቶችን ወደ የሰላም እና የተስፋ ድልድዮች እንዴት እንደሚቀይሩ ያሳያሉ ተብሏል።
 

07 Feb 2025, 17:12