የአፍሪካ የመገናኛ ባለሞያዎች የኢዮቤልዩ በዓል የሚዲያ ስልቶችን መልሶ ለማዋቀር የሚረዳ መሆኑን አስታወቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ለአንድ ዓመት የሚቆየው የተስፋ ኢዮቤልዩ የመጀመርያ ዝግጅቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመገናኛ ባለሞያዎችን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ፥ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (AMECEA) የተወጣጡ ብሔራዊ የመገናኛ ጽሕፈት ቤቶች መሪዎች ወደ ሮም ለመጓዝ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በላቲን “ኢንተር ሚሪፊካ” ወይም “ከአስደናቂ ነገሮች መካከል” በሚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1963 ዓ. ም. ይፋ የወጣውን ሐዋርያዊ ሠነድ እና “አንድነት እና ዕድገት” ወይም “ኮሙኒዮ እና ፕሮግረሲዮ” በሚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1971 ዓ. ም. የወጣውን ሐዋርያዊ የማኅበራዊ መገናኛዎች መመሪያ ተግባራዊነትን ለመገምገም የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1973 ዓ. ም. መሰብሰቡ ይታወሳል።
በምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት የማኅበራዊ መገናኛዎች አስተባባሪ የሆኑት አባ አንድሪው ካውፋ፥ “ከ50 ዓመታት በኋላ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የመገናኛ መስክን በተቆጣጠሩበት አውድ ውስጥ እነዚያን ስልቶች እንደገና ለማጤን ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢዮቤልዩ ጉብኝት የምሥራቅ አፍሪካ የመገናኛ ባለሞያዎችን ያጠናክራል
“የተስፋ ነጋዲያን” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የ2025 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች የስብከተ ወንጌል ዘዴዎችን ለማሳደግ ዕድል እንደሚሰጥ በኅብረቱ የማኅበራዊ መገናኛዎች አስተባባሪ አባ አንድሪው ካውፋ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
የኢዮቤልዩ ዓመት በተግባር እንዲገለጹ በሚፈለጉ አዳዲስ ሐዋርያዊ መገናኛ አቀራረቦች ላይ ግንዛቤን በማስጨበጥ የጳጳሳትን እና ብሔራዊ የካቶሊክ መገናኛ አስተባባሪዎች ችሎታን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚሁም ጋር ጉባኤው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጳጳሳትን እና አገር አቀፍ የመገናኛ አስተባባሪዎችን የሚያገናኝ ሲኖዶሳዊ አካሄድ ነው” ሲሉ አባ አንድሪው ካውፋ አስረድተዋል።
በጋራ ጉዞ ላይ የተመሠረተ ቅዱስ ዓመት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሕይወት ፈተናዎችን በተስፋ እንዲያሸንፉ እንደሚያበረታታት የገለጹት አባ አንድሪው ካውፋ፥ በተመሳሳይም “የብሔራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች የካቶሊክ ሚዲያ ሐዋርያነት ከሕዝቡ ጋር በጭብጡ ላይ በማስተንተን ለሰዎች ተስፋ ለመስጠት ቁርጠኞች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
የአፍሪካ የመገናኛ ባለሞያዎች በኅብረት መጓዝ
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ በምሥራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (AMECEA) ሥር የሚገኙ ብሔራዊ የመገናኛ ጽሕፈት ቤቶች መሪዎችን ብቻ ሳይሆን ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ወደ አንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚሰበስባቸው መሆኑን አስረድተዋል። አባ አንድሪው ካውፋ በማከልም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. የተከበረውን የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊክ ጳጳሳት ሲምፖዚየም (SECAM) ተነሳሽነት እና የፓን አፍሪካ የማኅበራዊ መገናኛ ኮሚቴ (ሲኢፓሲኤስ) የወርቅ ኢዮቤልዩን አስታውሰዋል።
በአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊክ ጳጳሳት ሲምፖዚየም (SECAM) ሥር የሚገኙ ስምንቱ ክልሎች የመገናኛ መዋቅሮችን እና ግንኙነቶችን ከሐዋርያዊ ዕቅድ ጋር በማዋሃድ ረገድ አንድ አይነት ገጽታ እንደሌላቸው ጠቁመዋል። ነገር ግን ይህ የኢዮቤልዩ ዓመት ከአፍሪካ የመጡ ተሳታፊዎችን እንደገና አንድ ላይ በማሰባሰብ አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን የመገናኛ መንገዶችን እንዲመረምሩ እና እንዲመክሩበት ሌላ ዕድል የሚሰጥ ነው” ያሉት አባ አንድሪው ካውፋ፥ “በሮም የሚካሄደውን የኢዩቤልዩ ስብሰባ ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ወይም በሌሎች የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ደረጃ ሌላ ስብሰባ ሊካሄድ እንደሚችል በመግለጽ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።