የጥር 04/2017 ዓ.ም ሰንበት ዘልደት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. ሮሜ 11፡25-36
2. 1ኛ ዮሐ. 4፡1-8
3. ሐዋ. 7፡17-22
4. ማቴ. 2፡1-12
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠየቃቸው።
እነርሱም “አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና” ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።
እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም ቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ (ማቴ 2፡1-12)።
የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ሰብአሰገል መሲሁን በደስታ ከመፈለግ አልታከቱም ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ” (ማቴ 2:2)። በጣም ረጅም የሚባል ጉዞ አድርገዋል። አሁን ደግሞ በታላቅ ጉጉት አዲስ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የተኛበትን ሥፍራ ትክክለኛ ቦታ ለማዋቅ በጉጉት ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። ይህንንም ሥፍራ በትክክል እንዲነግራቸው በማሰብ ወደ ንጉሥ ሄሮደስ ዘንድ ሄደው ይጠይቁታል። እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው።
ይህ በደስታ የተሞላ የሰብአሰግል ፍለጋ የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን ከነበራቸው የግድየለሽነት ባሐሪ ጋር ይቃረናል። እነርሱም በነብያት የተጻፉትን መጽሐፍት በሚገባ ያወቁ ስለነበረ ኢየሱስ የተወለደበት ትክክለኛ ሥፍራ የማወቅ አቅም ነበራቸው። በእዚህም ምክንያት እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፎአልና” (ማቴ. 2፡5) በማለት ተናገሩ። ይሁን እንጂ ወደ እዚያ ሥፍራ ለመሄድ አልተመቻቸውም ነበር። ቤተልሔም እነርሱ ከነበሩበት ሥፍራ በጣም ጥቂት ኪሎሜትሮች ርቃ የምትገኝ ሥፍራ ብትሆንም እነርሱ ግን መነቃነቅ አልፈለጉም ነበር።
ከእዚህም የከፋው ደግሞ የሄሮድስ ባሕሪ ነው። እርሱ ይባስ ብሎ ይህ የተወለደው ሕጻን ስልጣኑን የሚንጥቅበት መስሎት ስለተሰማው በጣም ደንግጦ ነበር። ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው (ማቴዎስ 2:7,8)። በእርግጥ ሄሮድስ ሕጻኑ የተወለደበትን ሥፍራ ማወቅ የፈለገው ለሕጻኑ ለመስገድ ፈልጎ ሳይሆን ነገር ግን ባለአንጣ አድርጎ ስለቆጠረው ሊገለው ፈልጎ ነበር እንጂ።
በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴዎስ 2፡1-12) በደስታ መፈለግ፣ ችልተኝነት እና ፍርሃት የተሰኙ ሦስት ባሕሪያት ተጠቅሰዋል። እኛም ከእነዚህ ከሦስቱ ባሕሪያት መካከል የትኛውን መውሰድ እንዳለብን መምረጥ ይኖርብናል።
የራስ ወዳድነት መንፈስ የኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ለመኖር መምጣቱ እንደ ማስፈራሪያ አድርገን እንድንቆጥር ይገፋፋን ይሆናል። በዚህም መንፈስ የተነሳ የኢየሱስን መልእክት ላለማዳመጥ ወይም ደግሞ እርሱ የሚነግረንን መልእክት ሰምተን ዝም ለማለት እንሞክራለን። አንድ ሰው ሰብዓዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ለምሳሌም በጣም ምቹ የሆኑ አመለካከቶችን፣ የክፋት ዝንባሌዎችን፣ በሚከተልበት ጊዜ ኢየሱስ እንደ እንቅፋት ሆኖ ይታየዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቸልተኝነት ፈተና ዘወትር በእኛ ውስጥ ይገኛል። ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን እያወቅን እርሱ አዳኝ እንዳልሆነ አድርገን፣ ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን ብናውቅም እንዳልሆነ አድርገን ለመኖር እንመርጣለን። ከኛ የክርስትና እምነት ጋር በጥብቅ ከመወዳጀት ይልቅ የዓለምን መርሆች እንከተላለን፣ ይህም የእብሪተኛነት ዝንባሌን የስልጣን እና የሐብት ጥማት እንዲኖረን ያደርጋል።
ይልቁኑም እኛ በደስታ እርሱን መፈለግ እንዳለብን እና በሁሉም ሁኔታዎችም ውስጥ ሳይቀር ኢየሱስን ለማግኘት ዝግጁ መሆን እንዳለብን ሰብአሰገልን ያሳዩንን አብነት ለመከተል ተጠርተናል። እሱን ለማምለክ መፈለግ፣ እርሱ ጌታችን መሆኑን እንድናውቅ እና እርሱን ለመከተል የሚያስችለንን ትክክለኛውን መንገድ የሚያመለክት እርሱ ብቻ መሆኑን ለማወቅ መሻት ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ኢየሱስ በእውነት እኛን ያድነናል፣ እኛ አስደሳች ሕይወት ልንኖር ይችላል፣ በእምነት በመፈለግ እና በተስፋ በእግዚአብሔርና በወንድሞቻችን ላይ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን።
ሰብአሰገል በኮከብ መሪነት ሕጻኑን ኢየሱስን እና እናቱን ማርያም ባገኙ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው ለሕጻኑ ያመጡትን ወርቅ፣ ዕጣን እና ከርቤ በስጦታ መልክ አቀረቡ ይለናል የዛሬው ቅዱስ ወንጌል። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የእነዚህን ሦስት ስጦታዎች ትርጉም ሲገልጹ ወርቅ ለንጉሥነርቱ፣ ዕጣን ለአምላክነቱ፣ ከርቤ ለሞቱ የቀረቡ ስጦታዎች እንደ ሆኑ ያስተምራሉ።
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ሰብአሰገል “ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ከተነገራቸው በኋላ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመለሱ” ይለናል። ይህ “በሌላ በኩል ወደ ቤታቸው ተመለሱ” የሚለው ቃል ለእኛም በጣም ጥልቅ የሆነ አስተምህሮ ይሰጠናል። በማነኛው መልክ ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር በምንገናኛባቸው ወቅቶች ሁሉ፣ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ቅዱሳን ምስጢራትን በምንሳትፍባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ በክፋት የተሞላውን የሕይወት መስመር በመቀየር አዲስ የሕይወት አቅጣጫ መከተል እንደ ሚኖርብን ያስተምረናል። ማነኛውም ዓይነት ከኢየሱስ ጋር የሚደረግ ግንኙነት፣ መነኛም ዓይነት ለኢየሱስ የሚደረግ ጸሎት ቀደም ሲል የነበረንን ለኢየሱስ እና ለባልንጀሮቻችን ተገቢ ያልሆነ የሕይወት መስመሮቻችንን እንድንቀይር እና በአዲስ የሕይወት ጎዳና ላይ እንድንመላለስ ኢየሱስ ይፈልጋል፣ የጋብዘናልም። ስለዚህ በእየለቱ ከኢየሱስ ጋር የምናደርገው ግንኙነት የሕይወት መስመራችንን በመቀየር ከእርሱ ፍላጎት ጋር በሚመጣተን መልኩ የኑሮ መስመራችንን ማስተካከል ይኖርብናል።
የእረኞችን እና የሰባአሰገልን ታሪክ ስንመለከት እነዚህ ሁለት ዓይነት የሥራ ዘርፍ ያላቸው ሰዎች አንደኛው በመልኣክት መሪነት ሌሎችም ደግሞ በኮከብ መሪነት ሕጻኑን ኢየሱስ ባገኙት ጊዜ እጅግ በጣም እንደ ተደሰቱ እንመለከታለን። ከዚህም ኢየሱስን መገናኘት ሁልጊዜም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ ደስታ በሕይወታችን ውስጥ እንዲከሰት ያደርጋል የሚለውን ስፊ ትምህርት እናገኛለን። በመቀጠል እነዚህ የተለያየ ዓይነት የሥራ ዘርፍ የነበራቸው ሰዎች እንደ ተባለው ሕጻኑን ኢየሱስን ካገኙት በኋላ ከሰገዱ እና እግዚኣብሔርን ካመሰገኑት በኋላ እዚያው አልቀሩም ወደ እየመጡበት ተመልሰው እንደ ሄዱ ቅዱስ ወንጌል ይገልጻል።
እኛንም ቢሆን ኢየሱስ ዛሬ የሚጠይቀን እርሱን መገናኘት ማለት እርሱን በመገናኘታችን ያገኘነውን ደስታ እና በረከት ይዘን ወደ መጣንበት በመመለስ ያንን በረከት ከሌሎች ጋር መቋደስ እንደ ሚገባን ከሰባአሰገል እና ከእረኞች ታሪክ እንማራለን ማለት ነው። ዛሬ የሰማነውን የእግዚኣብሔር ቃል ወደ እየመጣንበት በምንመለስበት ወቅት ያገኘንውን ደስታ እና በርከት ሁሉ ከሌሎች ጋር መቋደስ ይኖርብናል ማለት ነው።
በምድር ላይ ምጽሐተኞች ለሆንን ለእኛ ጨረቃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ በአማላጅነቷ ትርዳን። የእናትነት እገዛዋ ሁሉም ሰዎች እውነተኛ ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን በመከተል ዓለማችን በሰላም እና በፍትህ ጎዳና ላይ ይራመድ ዘንድ በአማላጅነቷ ትረዳን።
ምንጭ፣ በአባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ የተዘጋጀ-ቫቲካን