እህት አን አራቦሜ፥ በናሚቢያ ከሚገኙ ሌሎች ገዳማውያት ጋር ሲወያይዩ (በስተ ግራ) እህት አን አራቦሜ፥ በናሚቢያ ከሚገኙ ሌሎች ገዳማውያት ጋር ሲወያይዩ (በስተ ግራ) 

የናሚቢያ ካቶሊካዊ ገዳማውያት በአገሪቱ የነገረ-መለኮት ጥናት መንፈሳዊ ተቋም ከፈቱ

በናሚቢያ የሚገኙ ገዳማውያት እህቶች በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣውን የምንኩስና ጥሪ ታሳቢ በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረ-መለኮት እና መንፈሳዊ ሕይወት ማሰልጠኛ ተቋምን አቋቁመዋል። ይህም ሕይወቱን የሚመርጡ እህቶች በቂ ስልጠናን እንዲወስዱ ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል። ገዳማውያትን በዕውቀታቸው ብቁ ለማድረግ በናሚቢያ የመጀመሪያውን የነገረ-መለኮት ጥናት እና መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ተቋምን በማቋቋም እህት አን አራቦሜ ግንባር ቀደም ሆነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ተቋሙ በናሚቢያ መዲና ዊንድሆክ የሚገኙትን የልዩ ልዩ ገዳማውያት የበላይ አለቆችን በነገረ-መለኮት ትምህርት እና በመንፈሳዊ ስልጠናዎች ለማዘጋጀት መቋቋኑ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2023 ዓ. ም. ዓመታዊ የቤተ ክርስቲያን ስታቲስቲካዊ መረጃ መሠረት በአፍሪካ ውስጥ ጉልህ እና ቀጣይነት ያለው የገዳማውያት የምንኩስና ሕይወት ጥሪ ዕድገት መኖሩ ታውቋል። ዕድገቱን እንደ መልካም ስጦታ በመቀበል የነገረ-መለኮት ጥናት እና መንፈሳዊ ስልጠና መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋም ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል ለማይችሉ ገዳማውያት እህቶች ጥልቅ ፍላጎት እና ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ታውቋል።

የተገለሉትን እና በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በበቂ ሁኔታ አገልግሎትን ለመስጠት ሕይወታቸውን ለክርስቶስ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ገዳማውያት በነገረ-መለኮት ጥናት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በመንፈሳዊነት እና በአመራር ችሎታዎች ጠንካራ መሠረት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይታመናል።

የሎስ አንጀለስ የማኅበራዊ አገልግሎት እህቶች ማኅበር አባል የሆኑት እህት አን አራቦሜ፥ በናሚቢያ የሶፊያ የነገረ-መለኮት ጥናት እና መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ተቋም በመመሥረት በአፍሪካ ውስጥ ላለው ገዳማውያትን በብቃት የማሰልጠን አስፈላጊነት ምላሽ ሰጥተዋል።

“የማኅበራዊ አገልግሎት እህቶች ማኅበር ዋና ተነሳሽነት አባላት በቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ ተልእኮ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ስለ መንፈስ ቅዱስ እና በዓለም ውስጥ ስላለው ተግባር ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል። ተቋሙም የዚህ ተነሳሽነት መገለጫ ነው” ሲሉ እህት አን አራቦሜ አስገንዝበዋል።

በገዳማውያት እህቶች ጥሪ ወደ አፍሪካ ተመልሰዋል
እህት አን አራቦሜ በአሜሪካ ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ አፍሪካ የተመለሱት ለአፍሪካ ገዳማውያት አፍሪካዊ እሴቶችን እና የመንፈሳዊነት መርሆችን በማስተማር አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።

“ዘወትር በእግዚአብሔር የመጠራቴ ጠንካራ ስሜት ነበረኝ” ያሉት እህት አን አራቦሜ፥ ይህ ጥሪያቸው ወደ አፍሪካ በተለይም ወደ ናሚቢያ እና ደቡባዊ አፍሪካ እንዲመለሱ በማድረግ የሶፊያ ተቋምን ለመጀመር እንዳነሳሳቸው አስረድተዋል።

“በዚህ የአፍሪካ ክፍል ያሉ ገዳማውያትን በነገረ-መለኮት እና መንፈሳዊነት የማሰልጠን ዕድሉ ውስን ነው” በማለት የተናገሩት እህት አን አራቦሜ፥ “ስለ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ማለትም የክርስቶስን ብርሃን ለሌሎች ለማድረስ ብዙ ተሰጥኦ እና ብቁ ችሎታ ያላቸው ገዳማውያት መኖራቸውን ገልጸው፥ “ለእነዚህ ገዳማውያት በነገረ-መለኮት ጥናት፣ በመንፈሳዊነት እና በአመራር ችሎታዎች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፣ ይገባቸዋልም ሲሉ ተናግረዋል።

የሶፊያ ማሰልጠኛ ተቋም ትክክለኛ ተልዕኮም ይህ ነው” ያሉት እህት አን፥ ይህ መርሃ ግብር ቀደም ሲል ሌሎች ወጣት ልጃገረዶችን ስለ ምንኩስና ሕይወት የሚያስተምሩ ገዳማውያትን ሲያሰለጥን መቆየቱን ገልጸው፥ አነስተኛ የገንዘብ ክፍያን በመጠየቅ በምናባዊ የአሰራር ዘዴ የሚሰጥ ስልጠና በደቡብ አፍሪካ፣ በቦትስዋና፣ በዚምባብዌ እና በሌሴቶ የሚገኙ ሴቶችን ለአገልግሎት ሲያዘጋጅ መቆየቱን እህት አን ገልጸዋል።

በአገልግሎት እና ማኅበራዊ ፍትህ ላይ ከፍተኛ ዕውቀት አላቸው!
የቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊነት እና ነገረ-መለኮት ጥናት ላይ ከፍተኛ ልምድ እና እውቀት ያካበቱት እህት አን፥ በአሜሪካ ዊስኮንሲን ውስጥ በሚገኝ ማርኬቴ ዩኒቨርስቲ የቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊነት ትምህርት ተባባሪ ዳይሬክተር በመሆን ለስምንት ዓመት ሰርተዋል።

በናይሮቢ በሚገኝ ሄኪማ ኮሌጅ ውስጥ የሴት ምሁራን ፕሮግራም አባል የሆኑት እህት አን፥ በፋካልቲው ውስጥ ለተማሪዎች የአንትሮፖሎጂ፣ የመንፈሳዊነት እና የምንኩስና ሕይወት ትምህርቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በእንግሊዝ ከሚገኘው የሮሃምፕተን ዩኒቨርስቲ በስልታዊ ቲዎሎጂ እንዲሁም በቺካጎ ከሚገኘው የካቶሊክ ነገረ-መለኮታዊ ኅብረት በመንፈሳዊነት እና በአገልግሎት የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።

የእህት አን ተነሳሽነት በስኮትላንድ ግላስጎው ከሚገኘው የቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊ ማዕከል ጋር ሁለት አህጉራትን በማስተባበር ለአፍሪካውያን ገዳማውያት ባህላዊ ኑሮ እና የነገረ-መለኮት ጥናቶች መርሃ ግብርን በማስተዋወቅ ላይ ይገገኛል።

“በአፍሪካ ሴቶች መንፈሳዊ ሕይወት እና በቅዱስ ኢግናጢዮስ መንፈሳዊነት ላይ በማተኮር ለአገልግሎት፣ ለማኅበራዊ ፍትህ እና ለውጭ የትምህርት ዕድል ከፍተኛ ፍቅር አለኝ” የሚሉት እህት አን፥ የሲኖዶሳዊነት ሞዴልን በመከተል የአፍሪካ መሪዎችን ለማሰልጠን በፍላጎት መነሳታቸውን ገልጸው፥ የሲኖዶሳዊ እሴቶችን፣ መርሆችን እና ልምምዶችን በስልጠና መርሃ ግብራቸው ውስጥ ማካተታቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ገዳማውያትን ማበረታታት እና ክብራቸውን ማስመለስ
እህት አን እስካሁን በተጓዙት ጉዞ ላይ በማሰላሰል ለሶፊያ ተቋም ያላቸውን ጠንካራ ተስፋ ሲያጋሩ፥ “ይህ ተነሳሽነት የአፍሪካ ገዳማውያትን እና ማኅበረሰቦቻቸውን በፈጠራ እና በዐውደ-ጽሑፍ፣ በነገረ-መለኮታዊ አስተንትኖ፣ በስልጠና፣ በተሃድሶ፣ በመንፈሳዊ አጃቢነት እና በቅዱስ ኢግናጢዎስ የሱባኤ አደራረግ ለማበረታታት እና ክብራቸውንም ለማስመለስ የሚያስችል ዘዴ የሚያስተምር ተቋም ለማድረግ ህልም አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

እህት አን ገለጻቸውን ሲደመድሙ፥ ከገዳማውያት ጋር እንድጓዙ የጠራቸው እግዚአብሔር ከእርሳቸው እጅግ የሚበልጥ መሆኑን የተረዱበት አስደሳች ጀብድ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ ተልዕኮ እየተወጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

 

07 January 2025, 16:41