ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ  (AFP or licensors)

ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ፥ ክርስቲያኖች ወደ ቅድስት ሀገር ንግደት እንዲያደርጉ አሳሰቡ

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ክርስቲያኖች ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ንግደት እንዲጀምሩ ጋብዘው፥ “ይህም የቅድስት ሀገር ምዕመናን የዓለም አቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በቅድስት ሀገር ሕይወት ውስጥ ምልክት የተደረገበት የለውጥ ነጥብ ነው” ያሉት ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ ይህን የተናገሩት በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ቤተ ክርስቲያን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት እንደሆነ ታውቋል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካኅን ከሆኑት አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን ጋር ሆነው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ክርስቲያኖች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ንግደት ለመጀመር እቅድ እንዲያወጡ ጋብዘዋል።

“ያለፈው ዓመት አስቸጋሪ ዓመት ነበር” ያሉት ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ፥ ቅድስት ሀገር ችግር ውስጥ በወደቀችበት ወቅት ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ላደረገችው የጸሎት እና የአጋርነት ድጋፍ አድናቆታችንን መግለጽ እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት እሑድ ዕለት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ወዲህ ኢየሩሳሌም ሰላም ናት” ሲሉ ገልጸው፥ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ለቅድስት ሀገር ያላቸውን አጋርነት አሁንም በተጨባጭ እንዲገልጹ አሳስበዋል።

ብጹዕነታቸው በማከልም፥ “የተስፋ ምንጭ እና መነሻ፣ ከሞት የተነሳው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “በመሆኑም ወደዚህ ቅዱስ ሥፍራው ለመምጣት ድፍረት ሊኖር የሚገባው ጊዜ አሁን ነው” በማለት አሳስበዋል።

ንግደት እና ታላቁ የካቶሊክ ቤተሰብ
ከኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ጋር ሆነው የቪዲዮ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካኅን አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን በበኩላቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደባት፣ ወደ ሞተባት እና ከሞት ወደ ተነሳባት ቅድስት ምድር ንግደት የማድረግ አስፈላጊነትን አብራርተዋል።

አባ ፍራንችስኮች ፓቶን በቅዱስ መካነ መቃብሩ ፊት ቆመው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአካባቢው ክርስቲያኖች ወደ ሥፍራው የሚመጡ እንግዶችን ወይም ነጋዲያንን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ምክንያቱም በአካባቢው ያለው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ትንሽ በመሆኑ ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ ምዕመናን ሲያገኟቸው የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባልነት እና የዓለም ክርስቲያን ማኅበርሰብ አባልነት እንደሚሰማቸው በመግልጽ፥ ምዕመናን ሳይፈሩ በድፍረት ወደ ቅድስት አገር ንግደት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

 

21 January 2025, 16:41