የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ምዕመናን የጥምቀት በዓልን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት አከበሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የውይይት አስፈላጊነት በማጉላት የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጥር 10 እስከ 17/2017 ዓ. ም. ድረስ ተካሂዷል። ዓለም አቀፋዊ ዝግጅቱ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ እና ሥርዓተ አምልኮ ባህሎቻቸውን በማክበር ክርስትናን ለማበልጸግ ልዩ ጠቀሜታ ያለውን የወንድማማችነት ጥሪ አቅርቧል።
በዩክሬን ከጦርነቱ በኋላ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የታየውን መለያየት በመቃወም በኪየቭ በሚገኘው የግሪክ ካቶሊክ ካቴድራል ውስጥ ጥር 10/2017 ዓ. ም. በአብያተ ክርስቲያን መካከል የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ፥ በሥነ-ሥር ዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ “በትንሣኤ ላይ ያለን የእምነት አንድነት የተስፋችን ምንጭ ነው” ሲሉ ለተሰብሳቢዎች አስረድተዋል።
ወደ ቅድስት ሀገር የሚጓዙ ነጋዲያን
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን፥ ክርስቲያኖች ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ንግደት እንዲጀምሩ ግብዣቸውን አቅርበዋል።
አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን ያለፈው ቅዳሜ ጥር 10/2017 ዓ. ም. በቅዱስ መካነ መቃብር ፊት ቆመው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “ምዕመናን ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ንግደት እንዲጀምሩ” በማለት ግብዣቸውን አቅርበው እንደ ነበር ይታወሳል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በበኩላቸው፥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ምክንያት የጸጥታ ሁኔታ አሁን አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጠው፥ መተዳደሪያቸውን በነጋዲያኑ ላይ ላደረጉት የአካባቢው ክርስቲያን ቤተሰቦች ድጋፍ እንዲደረግ አደራ ሲሉ፥ አባ ፓቶንም በዚህ ኢዮቤልዩ ዓመት ክርስቲያኖች የተስፋ ነጋዲያን እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
የ2017 ዓ. ም. የጥምቀት በዓል
የግእዝ ስርዓተ አምልኮን የሚከተሉ የኢትዮጵያውያ እና ኤርትራ ክርስቲን ምዕመናን የጥምቀት በዓልን ከጥር 10-12/2017 ዓ. ም. ድረስ ማክብራቸውን ከመካከለኛው ምሥራቅ የወጡ ዜናዎች ገልጸዋል። ይህ ታላቅ የአምልኮ በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን እንደሚያስታውስ ይታወቃል።
በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ በጨርቅ የተጠቀለሉ ታቦቶችን የተሸከሙ ካህናት ከበርካታ ምዕመናን ጋር ሆነው ዑደት ሲያደርጉ ተመልክተዋል። ምእመናን ወደ ተባረከው ውሃ ድረስ ዑደቱ በማድረግ ጥምቀታቸውን ማደሳቸው ታውቋል።
በሃይማኖታዊ ዝማሬዎች የሚታጀበው ይህ የጥምቀት ሥነ-ሥርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በየዓመቱ የሚሰበስብ ሲሆን፥ ከ2011 ዓ. ም. ጀምሮ በዩኔስኮ እንደ ባህላዊ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።