በዮርዳኖስ የታነጸው አዲሱ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን መባረኩ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ለ15 ወራት ጦርነት ከተካሄደ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ታውቋል። ከእሁድ ጥር 11/2017 ዓ. ም. ጀምሮ የሚጸናው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነቱ 33 የእስራኤል ታጋቾች ነጻ እንዲለቀቁ የሚይደርግ እና ወደ 1,000 የሚጠጉ የፍልስጤም እስረኞች በምሕረት እንዲፈቱ የሚያደርግ እንደሆነ ታውቋል። በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ዜናውን በደስታ ተቀብሎ፥ “ሊለካ የማይቻለውን የሕዝብ መከራን እንደሚያስቆም ያለውን ተስፋ ገልጿል። የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት አክሎም የግጭቱ መንስኤዎች እንዲታወቁ ጠይቆ፥ ነጋዲያኑ ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ ጀምረው ለማየት ያለውን ፍላጎት ገልጿል።
በሊባኖ አዲስ ፕሬዝዳንት እና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጥ
ሊባኖስ የሪፐብሊኩን ፕሬዝዳንት አቶ ዮሴፍ አውን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ናዋፍ ሳላምን መምረጧ ታውቋል። አገሪቱ በምትመራበት የምርጫ ሥርዓት መሠረት ፕሬዝዳንቷ የማሮናውያን ሥርዓተ አምልኮን ከምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሱኒ የእስልምና እምነት እንደሆነ ታውቋል።
አቶ ዮሴፍ አውን በሞያቸው ወታደር ሲሆኑ እስከ አሁን ድረስ የሊባኖስ ጦር መሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ ናዋፍ ሳላም በበኩላቸው ዲፕሎማት እና የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የሠሩ መሆናቸው ታውቋል። ሊባኖስ ለ 2 ዓመታት ያለ ሥራ አስፈፃሚ ባለ ስልጣን ከቆየች በኋላ አሁን የፖለቲካ መረጋጋትን ለማምጣ ተስፋ እያደረገች ሲሆን፥ በሚቀጥሉት ቀናት መንግሥትን እንደምትመሠርት ይጠበቃል።
በዮርዳኖስ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ቡራኬ
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ኢየሱስ ክርስቶ በመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ የተጠመቀበት በሚባልበት በዮርዳኖስ አል-ማግታስ ወንዝ ዳርቻ የታነጸውን አዲስ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ዓርብ ጥር 2/2017 ዓ. ም. ባርከዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል። በዓለም ላይ ካሉት አንጋፋ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች መገኛ ከሆኑት መካከል አንዷ ዮርዳኖስ በአሁኑ ወቅት ከ11 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ መካከል ከ2 እስከ 4 በመቶ የሚሆኑት የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ታውቋል።