ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ፥ የፊሊፒን ምዕመናን በተስፋ አብረው እንዲጓዙ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቤተ ክርስቲያን የ2025 የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት በጀመረችበት በዚህ ወቅት፥ የፊሊፒን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን በተስፋ ጸንተው እንዲቆዩ ብርታትን በመመኘት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት ጥሪ በጽናት ለብሩህ ተስፋ ታማኞች ሆነው በሲኖዶሳዊ መንፈስ አብረው እንዲመላለሱ አደራ ብለዋል።
የፊሊፒን ምዕመናን ውስጣዊ ፅናት በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ጥልቅ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው
ብጹዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ በፊሊፒን የኢዮቤልዩ ዓመት መክፈቻን ምክንያት በማድረግ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ ፊሊፒናውያን ከፍርሃት ይልቅ ተፈጥሯዊ የተስፋ ዝንባሌ እንዳላቸው ገልጸው፥ ይህንን በአሥርት ዓመታት ውስጥ የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡ አስረድተዋል።
90 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የፊሊፒን ዜጎች ስለወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት እንዳላቸው የሚያሳየውን የዓመቱ መጨረሻ ዳሰሳን በመደበኛነት የሚያካሂደው የምርምር ድርጅት ግኝቶችን ጠቅሰዋል። ባለሙያዎቹ ይህንን ብሩህ ተስፋ ከፊሊፒን ምዕመናን ጥልቅ ሃይማኖተኛነት እና በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው እምነት ጋር እንደሚያዛምዱት ታውቋል።
“ከፍተኛ የተስፋ ስሜታችን ‘ሕይወት ካለ ተስፋ አለ’ ከሚለው ጽኑ እምነት ጋር የተያያዘ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ “በሕይወታችን ውስጥ ትግል እና ብስጭት ቢኖርብንም ‘እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነው፣ ዘወትር ይጥብቀናል ይንከባከበናል’ የሚለውን እምነት ይዘናል” ብለዋል።
በሌላ በኩል እንደ ድህነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ተፅዕኖ፣ የአእምሮ ጤና ችግሮች እና የፖለቲካ አለመረጋጋት የመሳሰሉ አንዳንድ ግልጽ እውነታዎች ለብዙ ሰዎች ተስፋቸውን ሊያጨልምባቸው እና ጠባብ ሊያደርግባቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የተስፋ ኢዮቤልዩ በእምነታችን ጽኑዎች ያደርገናል
“የጎርጎሮሳውያኑ 2025 የኢዮቤልዩ ዓመት በእምነት ለመጠንከር እና በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ያለንን ተስፋ እንድናጠናክር ጥሪን ያቀርብልናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ “የተስፋ ኢዮቤልዩ በእምነታችን ጽኑዎች ያደርገናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢዮቤልዩ ዓመት ተስፋን እንደ ዋና ጭብጥ የመረጡበት አቢይ ምክንያት፥ ሁሉም ሰው የወደ ፊት ሕይወትን ክፍት በሆነ መንፈስ፣ በሚታመን ልብ እና በአርቆ አሳቢነት አዲስ ጥንካሬ እና እርግጠኝነት እንዲያገኝ ለመርዳት ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ምዕመናን የኢዮቤልዩ ዓመትን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበው፥ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ መንፈሳዊ መታደስ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንደ ማኅበረሰብ በእምነት አብሮ የመጓዝን አስፈላጊነት በመግለጽ፥ “የኢዮቤልዩን ጸጋ ሳናባክን በሲኖዶሳዊነት የተጀመረውን በመንፈስ መታደስ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ወደ ጎን ማለት የለብንም” ሲሉ አሳስበዋል።
“ተስፋ ያለው ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ወይም ባዶ እንደሆነ አድርጎ አይመለከተውም። ተስፋ ያለው ሁሉ የሰውን ልጅ ጥማት የሚያረካ የሕይወት ውሃ ምንጭ ይጠጣል። እኛም የተስፋ ተጓዦች በመሆናችን በሲኖዶሳዊነት አብረን እንድንጓዝ ተጠርተናል” ብለዋል።
በተስፋ አብረን እንጓዛለን!
እንደ ተስፋ ተጓዦች በሲኖዶሳዊነት መንፈስ አብረን እንድንራመድ ተጠርተናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ በኃይለኛ የባሕር ሞገድ ውስጥ መስቀልን መከታ በማድረግ በጀልባ የሚጓዘውን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያሳየውን የኢዮቤልዩ ዓመት አርማ በማስታወስ በጻፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “እኛም ግንኙነታችንን ወደ መልካምነት ለመለወጥ በተጠራ ተመሳሳይ ጀልባ ላይ እንገኛለን” ሲሉ አሳስበዋል።
የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ካርዲናል ፓብሎ ቪርጂሊዮ ዴቪድ፥ “የጎርጎሮሳውያኑ 2025 መደበኛ የኢዮቤልዩ ዓመት የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች በቁምስናዎቻቸው እና በሀገረ ስብከቶቻቸው ውስጥ በሲኖዶሳዊነት የሚያድጉበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በተስፋ እና በፍቅር አብረን እንጓዛለን” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።