ባሕረ ጥምቀቱ ባሕረ ጥምቀቱ 

የጥር 11/2017 ዓ. ም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል እለተ ሰንበት ንባባት እና አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት
ኢሳ. 40፡1-5፣9-11
መዝሙር 104
ጢሞ. 2፡11-14፣3፡4-7
ሉቃስ 3፡15-16፣21-22

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሕዝቡም ሲጠብቁ ነበርና፥ ሁሉም በልባቸው ዮሐንስን በተመለከተ “እርሱ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አሰቡ፤ ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “እኔስ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ጠፍር መፍታት እንኳ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።

ሕዝቡም ሁሉ በተጠመቁ ጊዜ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል፤” የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ (ሉቃስ 3፡15-16፣21-22)።

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 3፡ 15-16, 21-22) ኢየሱስ ህዝባዊ ህይወት የጀመረበትን ሁኔታ ያሳየናል፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እና መሲሕ የሆነው በመጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሄዷል። ከሠላሳ ዓመታት ያህል የተደበቀ ሕይወት በኋላ፣ ኢየሱስ ራሱን በተአምር አላቀረበም፣ ወይም መድረክ ላይ ወጥቶ ትምህርት በማስተማር ተግባሩን አልጀመረም። በመጥመቁ ዮሐንስ ሊጠመቁ ከነበሩት ሰዎች ጋር ተሰልፏል። በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ ከመዝሙረ ዳዊት ተወስዶ በተነበበው መልእክት ላይ ሕዝቡ በባዶ ነፍስና በባዶ እግራቸው ሊጠመቁ እንደሄዱ ይናገራል። በባዶ ነፍስ እና ባዶ እግር ያለው ይህ የሚያምር አመለካከት ነው። ኢየሱስም የኃጢአተኞችን ችግር ይጋራል፣ ወደ እኛ ይወርዳል። ወደ ወንዙ ይወርዳል፣ እናም ወደ ቁስለኛው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በመግባት እርሱን ለመፈወስ እራሱን በውሃ ውስጥ እንዲጠመቅ ያደርጋል፣ እናም ከእኛ ጋር እራሱን በመቀላቀል በመካከላችን ይጠመቃል። እርሱ ከእኛ በላይ እንደ ሆነ አድርጎ ራሱን አያቀርብም፣ እንደ ህዝብ በባዶ እግሩ በባዶ ነፍሱ ወደ እኛ ይወርዳል እንጂ። እሱ ብቻውን አይመጣም፣ ወይም ከተመረጠ ልዩ መብት ካለው ቡድን ጋር አይመጣም። እርሱ በፍጹም እንዲህ አያደርግም። ከህዝቡ ጋር አብሮ ይመጣል። የሕዝቡ ነውና ከእነዚህ ትሑት ሰዎች ጋር ሊጠመቅ ከእነርሱ ጋር ይመጣል።

እስቲ አንድ አስፈላጊ ነጥብ ላይ እናሰላስል፣ ኢየሱስ ጥምቀት በተቀበለበት ቅጽበት መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሚለው “ይጸልይ ነበር” (ሉቃስ 3፡21) ይላል። ኢየሱስ ይጸልያል። ግን ለምን? እርሱ ጌታ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ እኛ ይጸልያል? አዎን! ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚለን ከሆነ ኢየሱስ የጸሎት ሰው እንደ ነበረ ደጋግሞ የነግረናል። በጸሎት ብዙ ጊዜ ያሳልፋል። በእያንዳንዱ ቀን መጀመሪያ ላይ፣ ብዙ ጊዜ በሌሊት፣ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት … ጸሎቱ ውይይት፣ ከአብ ጋር ያለ ግንኙነት ነው። ስለዚህ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ "ሁለት አፍታዎች" ማየት እንችላለን በአንድ በኩል በዮርዳኖስ ወንዝ አማካይነት ወደ እኛ እንደ ወረደ የሚያሳይ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ዓይኑንና ልቡን ወደ አብ ለጸሎት ሲያነሳ ያሳያል።

ይህ ለእኛ ትልቅ የሆነ ትምህርት ነው፣ ሁላችንም በህይወት ችግሮች እና በብዙ ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠምቀናል፣ አስቸጋሪ ጊዜዎችን እና ምርጫዎችን እንድንጋፈጥ ተጠርተናል። ነገር ግን መጨፍለቅ ካልፈለግን ሁሉንም ነገር ወደ ላይ ከፍ ማድረግ አለብን። ጸሎትም የሚያደርገው ይህንኑ ነው። ማምለጫ መንገድ አይደለም፣ ጸሎት አስማታዊ ሥነ ሥርዓት ወይም የተሸመደድ አጭር ግጥም አይደለም። በፍጹም እንዲህ አይደለም። ጸሎት እግዚአብሔር በእኛ እንዲሠራ የምንፈቅደው መንገድ ነው፣ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ እኛን ሊያነጋግረን የሚፈልገውን ለመረዳት፣ ጸሎት ወደ ፊት ለመሄድ የሚያስችል ጥንካሬ አለው። ብዙ ሰዎች መቀጠል እንደማይችሉ ይሰማቸዋል፣ እናም “ጌታ ሆይ፣ እንድቀጥል ጥንካሬን ስጠኝ” ብለው ይጸልዩ። እኛም ብዙ ጊዜ ይህንን አድርገናል። ጸሎት ይረዳናል ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስለሚያደርገን፣ እርሱን እንድንገናኝ መንገዱን ስለሚከፍትልን ነው። አዎን ጸሎት ልባችንን ለጌታ የሚከፍት ቁልፍ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው፣ ቃሉን ማዳመጥ ነው፣ ማምለክ ነው፣ በዝምታ መቆየታችን፣ እየደረሰብን ያለውን አደራ መስጠት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ኢዮብ ወደ እርሱ ማልቀስ ማለትም ሊሆን ይችላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከእርሱ ጋር መጨቃጨቅ ማለትም ሊሆን ይችላል። እንደ ኢዮብ ማልቀስ፣ እርሱ አባታችን ነው፣ በደንብ ይረዳናል። በፍፁም አይናደድብንም። ኢየሱስም ይጸልያል።

ጸሎት - በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በሚያምር ሁኔታ እንደ ተገለጸው ይህንን የሚያምር ምስል በመጠቀም "ሰማያት ተከፈቱ" (ሉቃስ 3፡21) ይለናል። ጸሎት ሰማያትን ይከፍታል፣ የህይወት ኦክሲጅንን ይሰጣል፣ በህይወት ችግሮች መካከል ንጹህ አየር እስትንፋስ እና ነገሮችን በሰፊው እንድንመለከት ያስችለናል። ከሁሉም በላይ በዮርዳኖስ ወንዝ የኢየሱስን ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዲኖረን ያስችለናል፡ እንደ የተወደዱ የአብ ልጆች ሆነን እንዲሰማን ያደርጋል። ስንጸልይ አብም በወንጌል ለኢየሱስ እንዳደረገው “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ” (ሉቃስ 3፡22) ይለናል። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን የጀመረው በጥምቀታችን ቀን ነው፣ እሱም በክርስቶስ ውስጥ እንድንጠመቅ ያደርገናልና፣ እንደ እግዚአብሔር ህዝብ አባላት፣ የተወደድን የአብ ልጆች እንድንሆን ይፈቅድልናል። የጥምቀታችንን ቀን በፍጹም አንርሳ! አሁን እያንዳንዳችሁን ልጠይቃችሁ? የተጠመቃችሁበት ቀን መቼ ነው? ምናልባት አንዳንዶቻችሁ አታስታውሱ ይሆናል። ይህ የሚያምር ነገር ነው፡ የተጠመቅክበትን ቀን ማስታወስ መልካም ነገር ነው፣ ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር የእግዚአብሔር ልጆች የሆንበት ዳግም ልደታችን ነውና! እናም ወደ ቤት ስትመለሱ የተጠመቃችሁበትን ቀን የማታውቁ ከሆነ እናትህን፣ አክስትህን፣ አያትህን ወይም የክርስትና እናት ወይም አባትህን "መቼ ነው የተጠመኩት?" ብላችሁ ጠይቁ፣ እናም ያንን ቀን ለማክበር፣ ጌታን ለማመስገን ያንን ቀን ሁሌም ቢሆን አስታውሱ። እናም ዛሬ በዚህ ጊዜ፣ እራሳችንን እንጠይቅ፡ ጸሎቴ እንዴት እየሄደ ነው? የምጸልየው ከልምድ የተነሳ ነው፣ ሳላስብ እጸልያለሁ፣ ቀመሮችን እያነበብኩ ነው ወይስ ጸሎቴ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ነው? እኔም ኃጢአተኛ፣ ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር፣ ተነጥዬ አላውቅም? ከእግዚአብሔር ጋር መቀራረብ፣ ከእርሱ ጋር በመነጋገር፣ ቃሉን እሰማለሁ? በየቀኑ ከምንሰራቸው ብዙ ነገሮች መካከል ጸሎትን ቸል አንበል፣ ለጸሎት ጊዜ እንስጥ፣ አጫጭር ልመናዎችን ብዙ ጊዜ በመደጋገም እንጠቀም፣ በየቀኑ ቅዱስ ወንጌልን እናንብብ። ሰማያትን የሚከፍት ጸሎት ነውና።

አሁን ደግሞ ሕይወቷን ለእግዚአብሔር በምስጋና ጽሎት ወደ ምታቀርበው ወደ እመቤታችን ማርያም በጸሎት እንመለስ።

 

18 January 2025, 10:55