ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የ2017 ዓ. ም. የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን!
'ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ' (ወደ ገላትያ ሰዎች 4፤4)።
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ክብራን ካህናት፣ ገዳማውያንና/ውያት፣ መላው ምዕመናንና የአገራችን ሕዝቦች፣ በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሙሉ፥ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማክበር የተዘጋጃችሁ ምዕመናንና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንኳን ለ2017 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ። ይህንንም የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ይህን መንፈሳዊ መልዕክት ሳስተላልፍላችሁ እስከዚች ዕለትና ሰዓት በደህና አድርሶን የልደት በዓልን ለማክበር ላበቃን አምላክ ምስጋና በማቅረብ ነው።
በየዓመቱ የልደት በዓልን እናከብራለን የጌታ ልደት ከሌሎች ልደቶች ይለያል። እንደምናውቀው የታላላቅ ሰዎችን ልደቶች ማክበር የተለመደ ነገር ነው። ለአንድ አካባቢ ሕዝብ ወይንም ለሰው ልጆች በሙሉ አንድ ቁምነገር ያበረከተ ሰው ይከበራል። በዚህም ክርስቶስ ምን አደረገ? ምን አስተማረ? ምን አመጣ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል። እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ማቅረብ የልደትን በዓል ትልቅነት እንድናስተውል ያደርገናል። የልደትን በዓል ስናከብር፤ የጌታን ልደት፤ የጌታን ጥምቀት፤ የጌታን ስብከቶች፤ የጌታን ታምራት፤ የጌታን ሕማማቱን፤ ሞትና ትንሣኤውን እያሰብን ሊሆን ይገባል።
የዛሬ በዓላችን ከቤተክርስቲያን ውጭም በቤተሰብም፣ በማኅበራችንም ሊንጸባረቅ ይገባል። በወንጌል ፈሪሳውያን በአብዛኛው የክርስቶስን ትምህርት ሲቃወሙ እናያለን። ከዚህ ምን እንማራለን? እንደ እነርሱ የምንሆንበት አጋጣሚዎች አሉ ወይ ብለን ሕይወታችንን እንመርምር። 'እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም' (ማቴ.18፡3) የሚለውን የጌታ ልደት ነው የምናከብረው። ሕጻናት በወላጆች ወይንም በአሳዳጊዎች ሥር ጥገኛ እንደሆኑ ሁሉ እኛም በእግዚአብሔር ሥር ጥገኛ መሆናችንን ስናውቅና ስንገነዘብ የክርስቶስ የልደት በዓል ይደምቃል፡፡ ልባችንን ያበራዋል ለደስታችን ሙላት ይሰጠዋል። ትልቅ ትርጉምም ይኖረዋል።
የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ሐዋርያት የዕለት ኑሮ ሥራቸውን ትተው ክርስቶስን ተከተሉ፣ በእርሱም ተማረኩ። የገና ልደት እንግዲህ የሚያምረው በእኛም ዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ክርስቶስ ምን ያህል ቦታ አለው ብለን ስንጠይቅ የደመቀ በዓል ይሆናል። ከበዓላችን ወደ ሕይወታችን፤ ከሕይወታችን ደግሞ ወደ በዓላችን በልባችን መመላለስ ያስፈልገናልና ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት ከሮም የተላከ የመቶ አለቃ "በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ' (ማቴ.27፡54) ብሎ መሰከረ። የልደት በዓል የእግዚአብሔር ልጅ የልደት በዓል መሆኑን እንድናስተውል ዕድል ሰጠን፡፡ በዚህም የክርስቶስ ልደት ከዝነኞች ሰዎች ልደት በላይ መሆኑን ያሳየናል። በአጭሩ ክርስቶስ ደስ የሚለውን ለማወቅና ለመፈጸም ስንፈልግ ነው የገና በዓል በልባችንና በማኀበራችን የሚደምቀው።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዘመን የማይወሰን ሆኖ በዘመናችን ውስጥ መጣ። የዘመን ባለቤትና የዘመን ፈጣሪ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ገባ። እኛ ግን እንደ ሰው ያለፈውን እናስታውሳለን። የሚመጣውን እንጠብቃለን፤ ካለፈው ዘመን ወይንም ካለፉት ጊዜያት የሚያበሳጩን ነገሮች ይኖራሉ። የሚቆጩንም ነገሮች ይኖራሉ። እንደዚሁም የሚመጣው ዘመን ያስፈራን አሊያም ያስጠነቅቀን ይሆናል። በእነዚህ ጊዜያት የሚያጽናናን ዛሬ ልደቱን የምናከብረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ምክንያቱም ያለፈውን ከቁጭት የሚያድነው ቁስልንም የሚፈውሰው እርሱ ነውና። እንደዚሁም የወደፊቱን አስመልክቶ ከስጋት የሚታደገን ዛሬ ልደቱን የምናከብረው ጌታ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ፥ 'በዚህ ተስፋ ድነናል' ይላል (ሮሜ 8፤24)። የሚያድነንና የሚያጽናናን በበረት የተወለደው ሕፃኑ ኢየሱስ ነው። በመልኩና በአርዓያው የፈጠረውን ሰው ሊጎበኝና ሊያድን የመጣው ወልደ አምላክ ነው።
በዘመናችን የሰው ልጅ ያለእግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን መፈፀም የሚችል ይመስለዋል። ነገር ግን ከዚሁም የተነሣ በጨለምተኝነትና በአፍራሽ ሐሳቦች ይዋጣል። የሕይወትን ትርጉም ያጣል። ያጣውንም ሰላም በማይሆኑ ጊዜያዊ ነገሮች ለመተካት ይሞክራል፣ የሥነ ምግባርን ዋጋ ይስታል፣ የማጋራትን ፀጋ ይነፍጋል፣ ከሰው ክብር ይልቅ ሥልጣንን፤ ክብርንና ምቾትን ይፈልጋል። ነገር ግን ምንም ቢያገኝ በመጠን መኖር ያቅተዋል፡፡ በቃኝ ማለትን ይረሳል፡፡ ለተራበውና ለተጎሳቆለው ወንድሙና እህቱ ማዘን ይሳነዋል፡፡ በእግዚአብሔር መልክና አምሳያ የተፈጠረው ወንድሙና እህቱ አያሳዝኑትም፤ ዳሩ ግን ያለ እምነት ያለ ተስፋና ፍቅር እሩቅ መሄድ አይቻልም፡፡ ለእግዚአብሔር ቦታ የማይሰጥ ግለሰብ ወይንም ማኅበረሰብ ለተስፋም ቦታ መስጠት አይችልም፡፡ የሰው ልጆች ፍልስፍና ገደብ አለው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ሲባረኩ ከእግዚአብሔር ሲመነጩ ግን እሩቅ ያደርሳሉ፡፡
የሰው ልጅ የተፈጠረው ለእውነተኛ ደስታና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡ የገና በዓልም የዚህ ምሥራች ነው። የደስታ ምንጭ ጌታ ደስታን ሊያበሥረን ብቸኝነታችንን ሊያጠፋ ተወለደ፡፡ ጨለማችንን የሚገፍ ብርሃን ተወለደ፣ አለማወቃችንን የሚሽር ጥበብ ተወለደ፡፡ ከራስ ወዳድነት የሚያድን ጌታ ሕይወትን ሊለግሰን ተወለደ፡፡ ፍርሃታችንን ሊያስወግድ አማኑኤል ተወለደልን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የምስራች ቤተሰቦቻችንን እንዲያጽናና በርና መስኮቶቻችንን እንክፈት፡፡ ይህንን የምስራች በልባችን ጓዳ ውስጥ እናስቀምጥ፡፡ የዘወትር የልባችን ሃብትና መዝገብ ይሁንልን፡፡ እንዲህ ከሆነ የጌታ ልደት የሕይወታችንን አቅጣጫ ይመራዋል፡፡
የተከበራችሁ ምዕመናን ይህ የልደት በዓል እምነታችን የሚጎለብትበት፤ ለፍትሕ የምንቆረቆርበት፤ ለተቸገሩ የምናዝንበት እንዲሆን እንፀልይ፡፡ ይህ የልደት በዓል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ይሁንልን፡፡እውነተኛ ደስታ ከእግዚአብሔር የሚገኝ ደስታ መሆኑን የምናስተውልበት ይሁን፡፡ የነቢዩ ኢሳያስ ትንቢት ሁልጊዜ በልባችን ውስጥ ይመላለስ፡፡
'ሕፃን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም ልዑል ይባላል ለመንግስቱም ስፋት ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም መንግስቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፡፡ ደግፎ በመያዝም ያፀናዋል፡፡ በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል አገሩንም ሁሉ ይገዛል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አባት ቅናት ይህን ያደርጋል' (ኢሳ.9.5-6)። ይህ የነቢዩ ኢሳይያስ መልዕክት በአንክሮ ሊታይ ይገባዋል፡፡ የልደት በዓል እራሳችንን እንድንጠይቅ ሊያግዘን ይገባል። የሰው ልጅ በእውቀት በቴክኖሎጂ በሌሎችም ነገሮች ማደጉ በራሱ ክፋት የለውም ጥያቄው ግን በሥነ ምግባር እና በመልካምነት ምን ያህል አደገ የሚለው ነው የሰው ልጅ ከጦርነት፤ ከጥላቻ፤ ከቅናት፤ ከግፍና ከሐሰት ምን ያህል ተላቀቀ ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ ካልሆነ ግን በእውነት አደገ እንዴት ማለት ይቻላል? የሰው ልጅ እራሱን እንዳልፈጠረ ሁሉ እራሱን ለማወቅ በዙርያው ያለውን ማጥናት አይበቃውም፤ ይልቁንም እራሱን ሊመረምር ይገባዋል፤ የሰው ልጅ ከሚገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ ከገባበት ገደል፣ ከተዘፈቀበት ማጥ፣ የሚያወጣው የልደት ባለቤት የሕይወት ምንጭ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ የሱንም ልደት ስናከብር ይህንን እያስተዋልን ይሁን፡፡ ከተወለደው ሕፃን ጋር በመሆን የሰው ልጅ ማደግ ይችላል ምክንያቱም የሰው ልጅ ብቻውን ቢጥር ሊፈጽመው የማይችለውን እንዲችል የሚያስችለው ጌታ መምጣቱን የሚገነዘብበት በዓል ነው፡፡
መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ 'ሰላም በምድር' የሚል የምሥራች ዜና በምድር ላይ መሰማቱ የሰላምን አስፈላጊነት በበለጠ አጉልቶታል፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ በዓለም ላይ በሰላም መኖር የሚችለው ሰላም ሊፈጠር የሚችልበትን የፍትሕና ርትዕ ተግባር በመፈፀም እንጂ በኃይልና በግዴታ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሌላውን እንደራስ ከማየትና አንድ ሰው በራሱ ላይ ሲደረግ የማይፈቅደውን ነገር በሌላ ላይ ለማድረግ ካለመፍቀድ የተሻለ የሰላም ጎዳና አይኖርም፡፡ ስለዚህ ለሰላም ኑሮ መሠረት የሆነው ይህ ፍትሕና ርትዕ በአገራችና ላይ ይሰፍን ዘንድ የቤተክርስቲያናችን የዘወትር ምኞትና ፀሎት ነው፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ሁሉም እኩል እንደመሆኑ መጠን በዚህች ለምለም ምድር ላይ ሰውን ያኖረው በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነውና፡፡ የክፋትና የጥላቻ ተልዕኮ ከአገራችን ጠፍቶ አገራችን ትባረክልን ዘንድ ቤተክርስቲያን ዘወትር ትፀልያለች፡፡ ስለሆነም ከአገራችን መከራና ችግር ሐዘንና ሰቆቃ ጦርነትና ስደት ተወግዶ በሕዝቦቻችን መካከል ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍንልን የሰላም አምላክ ለአገራችን ሰላሙን ፍቅሩንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡
የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በምናከብርበት በዚህ ወቅት የልደት በዓልን ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የሚያከብሩትን በጸሎት ማሰብ ተገቢ ነው በተለይም በማይናማር ሀገር ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን አልፎም ደግሞ ሀገራቸውን ለመጥቀም ብለው ለሥራ ከሀገር ወጥተው ታግተው የቀሩ ወጣቶችን እንድናስባቸው ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታቀርባለች። ከዚህ በተጨማሪም ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ምዕመናን መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ሕክምናን በአንድነት መውሰዳቸው በእምነት የሚደገፍ መሆኑን እያስታወስን ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ላይ አድሎና ማግለል እንዳናደርስባቸው አደራ ለማለት እወዳለሁ።
በመጨረሻም በዓሉ በመተሳሰብና በመረዳዳት የምናልፍበት፤ የታመሙት የሚድኑበት፤በጭንቀትና በመከራ ላይ የሚገኙትን እግዚአብሔር ሰላምንና መረጋጋትን እንዲሰጣቸው ፤ከአገራቸውና ከቄያቸው ርቀው በስደት ላይ ያሉትን እንዲያጽናናልን፤ በየማረሚያ ቤቶች ያሉትን እግዚአብሔር እንዲያስባቸው፣ ያዘኑትን እነዲያጽናናቸው፣ ወላጆቻቸውን ያጡትን ልጆች እነዲያበረታታልን፣ የሞቱትን በመንግስቱ እንዲቀበላችው እየተመኘን በዓሉን የሰላምና የደስታ በዓል ያድርግልን፡፡
የሰላም ንጉሥ የሆነው ሕፃን ኢየሱስ ለአገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፡፡ መልካም የልደት በዓል ለሁላችሁም ይሁንላችሁ!"
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን