ፈልግ

በማያንማር ካቺን ግዛት የአዲስ ጳጳስ ሹመት በማያንማር ካቺን ግዛት የአዲስ ጳጳስ ሹመት 

ብፁዕ ካርዲናል ቦ፥ ችግር በበዛበት የካቺን ግዛት አዲስ ጳጳስ በመሰየማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

የማያንማር ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ በሰሜን ምያንማር ካቺን ግዛት አዲስ የተሾሙት አቡነ ጆን ሙንግ ላ ሳምን ለእምነታቸው እና ለአገልግሎታቸው አመስግነው በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉትን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ዛሬ ሰማይ እና ምድር የእግዚአብሔርን ክብር ያውጃሉ፣ እግዚአብሔር ለሚያትኪና ሀገረ ስብከት አዲስ ሐዋርያዊ እረኛ ስለ ሰጠን ደስ ይበላችሁ!” ያሉት የእስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ለሁለት ጊዜያት ያገለገሉት ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ፥ አቡነ ጆን ሙንግን የማይትኪና ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው በመሰየማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በካቺን ግዛት ዜጎች ይሰቃያሉ፣ ይፈናቀላሉ!
በሰሜናዊ ማያንማር የሚገኘው እና ከቻይና ጋር የሚዋሰነው የካቺን ግዛት፥ የካቺን ብሔረሰብ በብዛት የሚኖሩበት እና ከእነዚህም መካከል አብዛኛው ክርስቲያን ማኅብረሰብ እንደሆነ ታውቋል። ግዛቱ በወርቅ እና ሌሎች ብርቅዬ የምድር ውስጥ ማዕድናት የበለፀገ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ወደ ቻይና የሚላኩ እንደሆነ ታውቋል። አካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ባለው አለመረጋጋት እና በማያንማር ወታደራዊ አገዛዝ እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል በዘለቀው የትጥቅ ግጭት ሕዝቡ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እና መፈናቀል ተዳርጓል።

የእግዚአብሔር ጊዜ ፍጹም ነው!
ብፁዕ ካርዲናል ቦ በአቡነ ጆን ሙንግን የጵጵስና ሹመት ላይ በማትኮር ባሰሙት ስብከት፥ “ይህ ቀን የመታደስ ቀን፣ የተስፋ በዓል እና ሁላችንም በኅብረት ተነሥተን በሰፊው የእግዚአብሔር እርሻ ላይ እንድንሠራ የተጠራንበት ቀን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ሐዋርያዊ እረኛን ለማግኘት ጸልያችኋል፣ ብዙ ጠብቃችኋል! ነገር ግን እግዚአብሔር ጩኸታችሁን ያልሰማው ይመስላችኋል?” ያሉት ካርዲናል ቦ፥ “ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ይህንን እውነት በድፍረት ላውጅ ፍቀዱልኝ። የእግዚአብሔር ጊዜ ፍጹም ነው፣ ጊዜው ሲደርስ ማንም ሊያቆመው አይችልም! ይህ ወቅት ጳጳስ የተሾመበት ብቻ ሳይሆን ለሀገረ ስብከታችን የአዲስ ጉዞ መባቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“እግዚአብሔር ጥሪው ግልጽ ነው!” ሲሉ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ቦ፥ “ መለያየትን ወደ ጎን በመተው አሮጌ ቁስሎችን በሚፈውስ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል በመሆን፥ በተለይም በዚህ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት በጌታ በመታመን እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።

ልባችንን በጥልቀት የሚነካ ታሪክ
“የአዲሱ ጳጳስ የአቡነ ጆን ሙንግ ላ ሳም የሕይወት ታሪክ ልባችንን በጥልቀት የሚነካ እና እምነታችንን የሚያነቃቃ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ቦ፥ “ትሑት በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የተወለዱ እና ሕይወትን በቀላል መንገድ በጽናት በመኖር፥ በናዝሬት የነበረውን የኢየሱስን ስውር ሕይወት የሚመስል፥ ሕይወታቸው ተራ የሚመስል ቢሆንም ነገር ግን በመለኮታዊ ኃይል የተሞላ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

አቡነ ጆን ሙንግ ላ ሳም በእግዚአብሔር ዘንድ በመታወቅ፥ ዓለም ሳያስተውለው ለዓመታት በጸጥታ አገልግለዋል” ያሉት ካርዲናል ቦ አክለውም፣ ብዙዎች ሊያመነቱ በሚችሉበት ዕድሜ ውስጥ የሕይወት ውጣውረዶችን ተሸክመው በመቆየት ለውጡን በድፍረት ተቀብለውታል” ሲሉ አስረድተዋል።

“የአቡነ ጆን ሙንግ ላ ሳም ሕይወት ዘመን የማይሽረውን እውነት ያውጃል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ቦ፥ እግዚአብሔር ለአገልግሎት ብቁ የሆኑትን አይመርጥም፤ ነገር ግን የሚመርጣቸውን ለአገልግሎት ብቁ ያደርጋቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል። 

ለካቺን ሕዝብ የተስፋ ብርሃን ናቸው!
“የአቡነ ጆን ሙንግ ላ ሳም አስገራሚ የጽናት እና የጸጋ ጉዞ ለካቺን ሕዝብ የተስፋ ብርሃን ነው” በማለት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ቦ፥ ከእግዚአብሔር አቅም በላይ የሆነ ችግር የለም፤ ለክብሩም ቀላል ሕይወት የለም፤ ለፍቅሩም የራቀ ህልም እንደሌለ ያስታውሰናል" ሲሉ አክለዋል።

በካቺን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በብዙ መልኩ በተለይም ለምእመናን እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ታላቅ ተሳትፎዋ ንቁ የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ካርዲናል ቦ ገልጸው፥ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የካቺን ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሚና፣ በጥልቅ ርኅራኄ በድፍረት እና ጥበብ ማስተማርን፣ መቀደስን እና ማስተዳደርን የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው” ስሉ አስረድተዋል።

ግጭት እና መፈናቀል
አንድ ጳጳስ ግጭት፣ መፈናቀል እና ችግር በበዛበት አካባቢ የክርስቶስን ብርሃን ወደ ሕዝቡ በማምጣት ሕይወታቸውን ለመገንባት ኃይል በማግኘት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ሊወጡት እንደሚገባ፥ ብፁዕ ካርዲናል ቦ አበክረው ተናግረዋል።

“ግጭት እና መፈናቀል ሕይወትን በሚያውክበት በካቺን ግዛት ውስጥ ጳጳሱ የተስፋ እና የእውነት ድምፅ እንዲሆኑ ተጠርተዋል” ያሉት ካርዲናል ቦ፥ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛው መልዕክት፥ “ቃሉን ስበክ፥ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ተግተህ ሥራ፥ ፈጽመህ እየታገሥህ እና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ፣ ምከርም” በማለት የመከረውን በማስታወስ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በታላቅ ትዕግስት እና ጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለሕዝብ መታገል
“የጳጳስ አስተምህሮ በቅዱስ ወንጌል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቦ፥ የካቺን ሕዝብ የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች፥ እንደ መፈናቀል፣ በአደንዛዥ እፅ ምክንያት የሚመጣ የሥነ-ምግባር ውድቀት እና በግጭት ምክንያት የሚከሰቱ ጥልቅ ቁስሎችን ከተግዳሮቶቹ ጋር ማገናዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህ አንፃር ምእመናን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ክብር አውቀው ለእርቅ እና ለፍትሕ እንዲሠሩ፣ እምነቱ ሳይበረዝ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ተራርቀው የሚገኙ ገጠራማ እና ሰፊ የካቺን መንደሮች በሚገኙበት አውድ ውስጥ ጳጳሱ የአካባቢው ተወላጆች የሆኑ መሪዎችን እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን በመመደብ የሕዝቡን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲጠብቁ እና አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎችንም ጭምር እንዲደርሱ ማስቻል አለበት” ብለዋል።

 

15 Jan 2025, 15:17