በምያንማር የሚገኙ ዜጎች እየደረሰባቸው የሚገኘው መከራ ይምያሳይ ምስል በምያንማር የሚገኙ ዜጎች እየደረሰባቸው የሚገኘው መከራ ይምያሳይ ምስል   (AFP or licensors)

ካርዲናል ቦ: 'እ.አ.አ 2025 ዓ.ም በምያንማር ሰላም የሚያብብበት ዓመት ይሁን' ማለታቸው ተገለጸ!

የምይናማር የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ቦ ሁሉም ወገኖች በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁከት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስበዋል፣ ለአራት ዓመታት የሚጠጋ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ አገሪቷ በከፍተኛ ውጥረት ላይ በመሆኗ እ.አ.አ 2025 ዓ.ም የሰላም አመት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቤተ ክርስቲያን የተስፋ ኢዮቤልዩ አመት ስትጀምር፣ የማይናማር ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ አዲሱ ዓመት ለአራት ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ድምዳሜ ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ልባዊ ተስፋ ገልጸዋል።

እ.አ.አ 2025 ዓ.ም በሁሉም ምያንማር እና በሁሉም አካባቢዎች ሰላም የሚያብብበት ዓመት ይሁን” ሲሉ የያንጎን ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የኤዥያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለአዲሱ ዓመት በላኩት ምልእክት ገልጿል።

በምያንማር ወደ አራት ዓመታት የሚጠጋ የእርስ በርስ ጦርነት

 ምያንማር እ.አ.አ ከየካቲት 1/2021 ዓ.ም ጀምሮ በሁከት ውስጥ ትገኛለች፣ ወታደሩ በሕዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡትን አውንግ ሳን ሱ ኪ እና በእርሳቸው ብሄራዊ ዴሞክራሲ ሊግ የሚመራውን የተመረጠ ሲቪል መንግስት ከገለበጠ እና የዲሞክራሲ ደጋፊ ሰልፎችን በሃይል ከጨፈጨፈ በኋላ፣ በመላ አገሪቱ ሕዝቡን ያሳተፈ እንዲሁም በርካታ ብሔረሰቦችን ያቀፈ የትጥቅ ትግል መጀመሩ ይታወሳል።

ከመፈንቅለ መንግስቱ ጀምሮ ከ6,000 በላይ ንፁሀን ዜጎች በፀጥታ ሃይሎች ሲገደሉ ከ28,000 በላይ የሚሆኑት ታስረዋል፣ ከነዚህም መካከል አውንግ ሳን ሱ ኪ 14 የወንጀል ክሶች ጨምሮ አመጽ ከማነሳሳት እና ከምርጫ ማጭበርበር እስከ ሙስና ድረስ ተጠርጥረው የ27 አመት እስራት ተፈርዶባቸው በእዚያው በእስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ በቻይና እና በሩሲያ ድጋፍ የሚያገኘው የማይናማር ጦር ከተለያዩ ጎሣ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ ሽንፈትን አስተናግዷል።

የመንግስታቱ ድርጅት በምያንማር የሚገኘውን ጦር “ስልታዊ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ ብዙዎቹ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” በመፈጸሙ አውግዟል።

ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ሰላማዊ ዜጎችን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

በመልእክታቸው ላለፉት አመታት ዕርቅ እንዲደረግ ደጋግመው የጠየቁት ካርዲናል ቦ ምያንማር ክብሯን እና ተስፋዋን ለማስመለስ የምታደርገውን ራዕይ ገልጸው እንደነበር የኡካ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሁከትና ብጥብጥ በአስቸኳይ እንዲቆምና ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ህጻናትን ለመጠበቅ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቋል፣ “ምንም ዓይነት ህይወት እንዳይቀጠፍ፣ የትኛውም ማህበረሰብ እንዳይገለል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በምያንማር የሚገኘውን ጦር ሰራዊቱን በጦርነት ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ የፈጸሙ ወንጀሎችን በማውገዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው፣ ግጭቱ ከ 3.3 ሚሊዮን በላይ ንፁሀን ዜጎችን ማፈናቀሉ እና ከ 54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዲኖሩ አድርጓል።

እርቅ እና ፍትህ እንደ የሰላም መንገድ

ብፁዕ ካርዲናል ቦ ወጣቶች “የሰላም መሐንዲሶች ናቸው” ሲሉ ሀገሪቱ አፋጣኝ ዕድሎችንና ትምህርትን መስጠት እንዳለባት አሳስበዋል። ይህን በማድረጋቸው፣ “ሕይወታቸውን ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ነፍስ መልሰው እንዲገነቡ ኃይል እንሰጣቸዋለን” ብሏል።

የበርማ ጳጳሳት እርቅን የሰላም መንገድ አድርገው ጠቁመዋል። "እርቅ ሂደት ብቻ አይደለም፣ ምርጫ ነው - ከሥቃይ በላይ መውደድ፣ ከጥፋት ባሻገር የመገንባት ምርጫ ነው” ብሏል።

ፍትህ እና ክብርን ማስፈን ወደ ሰላም ያመራል ብለዋል ካርዲናል ቦ። "እውነተኛ ሰላም ከጦርነት አለመኖር ይበልጣል፣ የፍትህ፣ የጸጥታና የሁሉም ክብር መኖርን ያሳያል” ብለዋል። "በእምነት መሰረት ላይ የተገነባ፣ በርህራሄ የተሞላ እና በተስፋ የሚደገፍ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ሰላምን ለማምጣት የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አለመሳካቱ

ከአካባቢው ቤተ ክርስቲያን እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም የበርማ ወታደራዊ ጁንታ በብሔረሰቦች ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና ስቃይ ለማርገብ ምንም አይነት ምልክት አላሳየም ፣በተለይ የክርስትና እምነት ተከታዮች እና ባማር በሚበዙባቸው ክልሎች፣ በካያህ እና በቺን ግዛቶች የሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በአየር ድብደባ እና በመድፍ ተደምስሰው በሺዎች የሚቆጠሩ ለስደት ተዳርገዋል።

እስካሁን የተካሄዱት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሁሉ በተለይም የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር (ASEAN) ግጭቱን ማስቆም ባለመቻላቸው እና እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም ጁንታው ምርጫ ለማካሄድ የገባው ቃል ብዙ ጥርጣሬዎችን ፈጥሯል። በሌላ በኩል፣ ሀገሪቱ ወደ ብዙ ጎሳዎች መከፋፈሏ ወደ ባልካናይዜሽን አይነት ሊያመራ ይችላል፣ ይህም ወደፊት ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ቢመለስም ወደ አንድነት መምጣት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የቅርብ ጊዜ ምህረት

ይህ በንዲህ እንዳለ፣ እ.አ.አ በጥር 4/2025 ዓ.ም. ወታደራዊው መንግስት የደቡብ ምስራቅ እስያ ብሔር የነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ ወደ 6,000 የሚጠጉ እስረኞችን እንደሚፈታ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ከእስር መፈታቱ ኦንግ ሳን ሱ ኪን እንደሚጨምር የሚያሳይ ምንም ምልክት አልነበረም።

 

09 January 2025, 17:00