ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “የሥርዓተ ጾታ ትምህርት አስፈላጊነት”

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “የሥርዓተ ጾታ ትምህርት አስፈላጊነት”

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “ለሥነ ልቡና፣ ለትምህርትና ለምርምር ሳይንሶች ተገቢውን ክብደት በመስጠት ለአዳጊ ሕጻናትና ወጣቶች አዎንታዊና ጥንቃቄ የተሞላበት የሥርዓተ ጾታ ትምህርት የመስጠትን” አስፈላጊነት ገልጾአል። ስለሆነም፣ የትምህርት ተቋሞቻችን ይህንን ተግዳሮት ለመሸከም ብቁ ስለ መሆናቸው ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ሥርዓተ ጾታ በተናቀበትና በደኸየበት ዘመን የሥርዓተ ጾታ ትምህርትን ጉዳይ ማንሳት ቀላል አይደለም። ስለሆነም ጉዳዩ የሚታየው ከሰፊ የፍቅር ትምህርትና እርስ በርስ ከመሰጣጣት መዋቅር አንጻር ብቻ ነው። በዚህ መልኩ፣ ሥርዓተ ጾታ የሚነገርበት kንk የደኸየ ሳይሆን ደማቅና የዳበረ ይሆናል። ወሲባዊ ፍላጎትም ለደስታና ለፍቅራዊ ግንኙነት ዋጋ ያላቸው ችሎታዎችን ለማዳበር በሚያስችል መልኩ ራስን በማወቅና ራስን በመቆጣጠር ሂደት ሊመራ ይችላል።

የሥርዓተ ጾታ ትምህርት የሕጻናትና ወጣቶችን የብስለት ደረጃ ያገናዘብ መረጃ የሚሰጥ መሆን አለበት። መረጃው በተገቢው ጊዜና ለዕድሜአቸው በሚስማማ አኳኋን መቅረብ ይኖርበታል። ሕጻናትና ወጣቶች የአዳዲስ አስተሳሰቦችና ምክረ ሐሳቦችን ጥቃት፣ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ጎርፍና ወሲባዊነትን የሚያጣምሙ የቅስቀሳ ጫናዎችን በጥንቃቄ የመመርመር ችሎታቸውን የሚያዳብሩበት ድጋፍ ሳይኖራቸው አሃዛዊ መረጃዎችን ብቻ በእነርሱ ላይ ማብዛት ፋይዳ የለውም። ወጣቶች ለዕድገታቸውና ለብስለታቸው የማይጠቅሙ መልእክቶች ናዳ እንደሚወርድባቸው መገንዘብ ይገባቸዋል። አዎንታዊ ጫናዎችን ለይተው እንዲያውቁና እንዲሹ፣ በአንጻሩ የማፍቀር ችሎታቸውን የሚያሰናክሉ ነገሮችን እንዲጸየፉ መርዳት ያስፈልጋል። ከዚህ ሌላ፣ “ሕጻናትንና ወጣቶችን ከወሲባዊነት ርእሰ ጉዳይ ጋር ስናስተዋውቅ አዲስና ይበልጥ ተገቢነት ያለውን kንk መጠቀም” ይኖርብናል።

ጤናማ የትህትና ስሜትን የሚያዳብር የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ትልቅ ዋጋ ቢኖረውም፣ ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ትህትናን ያለፈው ዘመን ቅርስ አድርገው ይቆጥሩታል። ትህትና የራሳችንን ምሥጢር የምንጠብቅበትና ራሳችንን የሌሎች መገልገያ መሣሪያ ከመሆን የምንከላከልበት የተፈጥሮ ዘዴ ነው። የትህትና ስሜት ከሌለ፣ ፍቅርና ወሲባዊነት የማፍቀር ችሎታችንን ወደሚያዛባ ወሲባዊ ትምክህትና ጤናማ ወዳልሆነ ባሕርይ ደረጃ ዝቅ ሊል፣ ወደ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ወይም ሌሎችን ወደሚጎዱ የጾታ ሁከቶች ሊያመራ ይችላል።

ብዙውን ጊዜ፣ የሥርዓተ ጾታ ትምህርት በዋናነት “ጤናማ ወሲብን” በመለማመድ “ራስን መጠበቅን” ይመለከታል። እነዚህን የመሰሉ አባባሎች፣ በመጨረሻ የሚወለደው ልጅ ሊከላከሉት የሚገባ ጠላት ይመስል፣ ለወሲባዊነት ተፈጥሮአዊ የተዋልዶ ግብ አሉታዊ አመለካከት የሚሰጥ መልእክት ያስተላልፋሉ። ይህን የመሰለ አስተሳሰብ በመቀበል ፈንታ ራስን ማምለክንና ጭካኔን ያራምዳል። ስለዚህ፣ ወጣቶች ለጋብቻ የሚያበቃ ተገቢ የሆነ ብስለት፣ እሴት፣ የጋራ ቁርጠኝነትና ግብ ያላቸው ይመስል፣ በገዛ ሰውነታቸውና ምኞታቸው እንዲማረኩ መጋበዝ ምን ጊዜም ቢሆን ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ይህ አካሄድ ወጣቶች ሌሎች ሰዎች የራሳቸው ፍላጎት ወይም ውስንነት ማርኪያ መሣሪያ አድርገው በዘፈቀደ እንዲጠቀሙባቸው ያበረታታቸዋል። ስለዚህ ዋናው ነገር፣ ወጣቶች ለተለያዩ የፍቅር መገለጫዎች፣ የጋራ እሳቤዎችና እንክብካቤዎች እንዲሁም ለፍቅራዊ ክብርና ጥልቅ ትርጉም ላለው ተግባቦት ትኩረት እንዲሰጡ ማስተማር ነው። እነዚህ ሁሉ፣ ይፋ ቃል ኪዳን ከተገባ በኋላ፣ ሰውነታቸውን በስጦታ በማቅረብ ረገድ ለሚገለጽ ራስን ሙሉ ለሙሉና በለጋስነት ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጉአቸዋል። ስለዚህ፣ በጋብቻ የሚገለጽ ወሲባዊ አንድነት በቀደሙት ነገሮች ሁሉ የዳበረና ሁሉን ያካተተ የዝግጁነት ማሳያ ምልክት ይሆናል።

ወጣቶች “ወሲባዊ ስበት ለጊዜው ስለ አንድነት የተሳሳተ እምነት ያሳድራል፤ ሆኖም ይህ ‘አንድነት’ ፍቅር ከሌለበት፣ ሁለት የማይተዋወቁ እንግዶችን እንደ ተራራቁ ያስቀራቸዋል” በሚሉ ሁለት ብሂሎች መደናገር የለባቸውም። አካላዊ ንኪኪ ራስን በእውነት አሳልፎ ከመስጠት አኴኳያ ወሲባዊ ፍላጎትን ለመተርጎምና ለማስተላለፍ የሚረዳ ትዕግሥትን የተላበሰ ልምምድን ይጠይቃል። ሁሉን ነገር ባንዴ መስጠት ያስፈልጋል ብለን ካሰብን፣ ምንም ሳንሰጥ እንቀራለን። ወጣቶች ምን ያህል በቀላል ሊቆስሉ የሚችሉና ግራ የተጋቡ መሆናቸውን ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ፣ ፍቅርን በሚያሳዩበት መንገድ አለመብሰላቸውን እንዲያራዝሙ ማበረታታት ሌላ ነገር ነው። ነገር ግን፣ ዛሬ ስለ እነዚህ ነገሮች የሚያወራ ማነው? ለወጣቶች ትኩረት የመስጠት ችሎታ ያለው ማነው? ለታላቅና ለጋስ ፍቅርስ ማን ያዘጋጃቸዋል? ስለዚህ፣ የሥርዓተ ጾታ ትምህርትን በተመለከተ ገና ብዙ ይቀራል።ወጣቶች ለራሳቸው ብቻ ትኩረት ከመስጠት አልፈው ለሌሎችም ግልጽና ሌሎችን ተቀባይ ይሆኑ ዘንድ የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ለልዩነት አክብሮትና አድናቆት መስጠትንም ሊያካትት ይገባል። ግለሰቦች የሚያጋጥሙአቸውን ችግሮች ከመረዳት ባሻገር ወጣቶች የራሳቸውን ሰውነት እንዳለ እንዲቀበሉ ማረበረታታት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም “በራሳችን ሰውነት ላይ ሙሉ ሥልጣን አለን ብሎ ማሰብ፣ ብዙውን ጊዜ በተፈጥሮ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለን ወደሚለው አስተሳሰብ ሊለወጥ ይችላል… ተባዕታዊ ወይም እንስታዊ ሰውነታችንን ማድነቅ፣ ከእኛ ከሚለዩ ሰዎች ጋር ስንገናኝ ስለ ራሳችን ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳል። በዚህ ዐይነት፣ የፈጣሪ እግዚአብሔር ሥራ የሆነውን የሌላውን ወንድ ወይም ሴት ልዩ ስጦታዎች በደስታ ለመቀበልና የጋራ እርካታ ለማግኘት እንችላለን”። ራስን ብቻ ከመውደድና ለራስ ብቻ ትኩረት ከመስጠት ነጻ መሆን የምንችለው ልዩ የመሆንን ፍራቻ በማስወገድ ብቻ ነው ። የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ወጣቶች ሰውነታቸውን እንዳለ እንዲቀበሉና ‹‹ምን መደረግ እንዳለበት ባለማወቅ ምክንያት የራሳችንን የጾታ ልዩነት የመሰረዝ›› ሰበብን እንዲከላከሉ ሊረዳቸው ይገባል።

የተባዕታዊ ወይም እንስታዊ ማንነታችንን ቅርጽ መቀየር የሥነ ሕይወታዊ ወይም የሥነ ባሕርይ ምክንያቶች ውጤት ሳይሆን፣ የብዙ መሠረታዊ ነገሮች ማለትም የፀባይ፣ የቤተሰብ ታሪክ፣ የባህል፣ የልምድ፣ የትምህርት፣ የጓደኞች፣ የቤተሰብ አባላትና የታዋቂ ሰዎች ግፊት እንዲሁም የሌሎች የሕንጸት ሁኔታዎች ድምር ውጤት እንደ ሆነ መዘንጋት አንችልም። ወንድን ወይም ሴትን ከእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ መለየት እንደማንችል የታወቀ ነው። ምክንያቱም ይህ ከራሳችን ውሳኔዎችና ተሞክሮዎች ሁሉ ስለሚቀድምና ችላ ማለት የማንችላቸው ሥነ ሕይወታዊ ነገሮች በመኖራቸው ነው። ሆኖም፣ ወንድነት ወይም ሴትነት ጥብቅ የሆኑ ፍረጃዎች አለመሆናቸውም ይታወቃል። ለምሳሌ፣ የባልን የወንድነት ሥራ ከሚስት የሥራ ሰሌዳ ጋር ማጣጣም ይቻላል። የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ወይም ልጆችን የማሳደግ አንዳንድ ግዴታዎችን መወጣት የእርሱን ወንድነት አያሳንሰውም፤ ወይም ውድቀትን፣ የኃላፊነት መጓደልን ወይም ውርደትን አያመለክትም። ሕጻናት የአባትን ክብር የማይቀንሱ እነዚህን የመሰሉ ጤናማ “ልውውጦች” የተለመዱ መሆናቸውን እንዲያውቁ መርዳት ያስፈልጋል። ግትር የሆነ አቀራረብ ወንድነትን ወይም ሴትነትን ከመጠን በላይ ያጋንናል። ይህም ሕጻናትና ወጣቶች በተክሊል ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ ተዋህዶ ያለውን እውነተኛ ተደጋጋፊነት እንዲያደንቁ አያደርጋቸውም። ይህን የመሰለ ግትርነት በበኩሉ፣ የግለሰብን ችሎታ አያዳብረውም፤ ለምሳሌ፣ ሥነ ጥበብ ወይም ውዝዋዜ የወንድ፣ አመራር የሴት የሙያ መስክ አይደለም ብሎ እስከ ማሰብ ሊያደርስ ይችላል። ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይግባውና ይህ አስተሳሰብ አሁን ተለውጦአል። ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ጎደሎ አስተሳሰቦች አሁንም ሕጋዊ ነጻነትን ይወስናሉ፣ የሕጻናትንም የልዩ ስብእናና የእምቅ ችሎታ እድገትን ያደናቅፋሉ።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 280-286 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ


 

18 January 2025, 15:27