ፍቅር በቤተሰ ውስጥ፥ “የቤተሰብ ሕይወት እንደ ማስተማሪያ አካባቢ”
ቤተሰብ ነጻነትን በጥበብ መጠቀምን የምንማርበት የሰው ልጅ እሴቶች ቀዳሚ ትምህርት ቤት ነው። አንዳንድ ዝንባሌዎች በልጅነት ዘመን ስለሚዳብሩና ሥር ስለሚሰዱ፣ በአንድ ልዩ እሴት በመማረክ ወይም አንዳንድ ድርጊቶችን በመጥላት ረገድ እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ አብረው ይኖራሉ። ብዙ ሰዎች አንድን ነገር የሚያስቡትና የሚያደርጉት ካሳለፏቸው ዓመታት ከራሳቸው ያዋሄዱት ወይም የቀሰሙት ትምህርት ትክክል መስሎ ስለሚሰማቸውና “የተማርኩት እንዲህ ነው፤ ማድረግን የተማርኩት ይህንን ነው” ብለው ስለሚያስቡ ነው። በቤተሰብ ውስጥ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ከሚተላለፉ አንዳንድ መልእክቶች ትችትንም መማር እንችላለን። በአሳዛኝ ሁኔታ፣ አንዳንድ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ወይም የማስታወቂያ ዐይነቶች ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሰረጹ እሴቶችን አሉታዊ በሆነ መልኩ ያፍናሉ፣ ያጎድፋሉ።
ሥጋትና ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት በሰፈነበት ዘመናችን፣ ከቤተሰቦች ዓበይት ተግባራት አንዱ ተስፋ ማድረግን ማስተማር ነው። ይህ ማለት ግን ሕጻናት በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች እንዳይጫወቱ መከልከል አይደለም። ይልቁንም ሕጻናት ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታቸውን የሚያዳብሩባቸውን መንገዶች መፈለግና የኤሌክትሮኒክ መረጃዎች ፍጥነት ሁሉንም የኑሮ ሁኔታ አይመለከትም ብለው እንዲያስቡ መርዳት ነው። ፍላጎትን ማዘግየት ማለት መከልከል ሳይሆን ተፈጻሚነቱን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ማለት ነው። ሕጻናት ወይም አዋቂዎች አንዳንድ ነገሮችን ማዘግየት እንዳለባቸው ካላስገነዘቡአቸው፣ ጊዜያዊ ፍላጎታቸውን በማርካት ይጠመዳሉ፣ ‹‹ሁሉንም ነገር አሁኑኑ” የሚለውን መጥፎ ምግባር ያዳብራሉ። ይህም ነጻነትን የሚያዳክም እንጂ የማይጠቅም ትልቅ ቅዠት ነው። በሌላ በኩል፣ ትክክለኛው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ አንዳንድ ነገሮችን ማዘግየትን ስንማር፣ ራስን መግዛትንና ከስሜታዊ ግፊት መላቀቅን እንማራለን። ሕጻናት ስለ ራሳቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲገነዘቡ፣ ስለ ራሳቸው ያላቸው ክብር ይጨምራል። ይህም በበኩሉ የሌሎችን ነጻነት እንዲያከብሩ ትምህርት ይሆናቸዋል። ይህ ማለት ግን ሕጻናት እንደ ዐዋቂዎች እንዲያደርጉ መጠበቅ እንዳይደለ ወይም ኃላፊነት በሚሰማው ነጻነት የማደግ ችሎታቸውን መናቅ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በጤናማ ቤተሰብ ውስጥ ይህ የመማር ማስተማር ሂደት ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው የጋራ ሕይወት በሚጠይቀው መሠረት ነው።
ከሌሎች ጋር መገናኘትን፣ ሌሎችን ማዳመጥንና ለሌሎች መጋራትን፣ ትዕግሥትንና አክብሮትን፣ እርስ በርስ መረዳዳትንና አብሮ መኖርን የምንማረው በዚያ ስለ ሆነ፣ ቤተሰብ ለማኅበራዊ ኑሮ ቀዳሚ አካባቢ ነው። የማስተማር ሥራ ዓለምና ኅብረተሰብ ጭምር ቤታችን መሆናቸውን እንድንገነዘብ ማድረግ ነው፤ በዚህ ሰፊ ቤት ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለብን እንማርበታለን። በቤተሰብ ውስጥ፣ ቅርበትን፣ እንክብካቤንና መከባበርን እንማራለን። ገዳይ ከሆነው ራስን ብቻ ከመውደድ ስሜት ተላቅቀን የእኛ እንክብካቤ፣ ቸርነትና ፍቅር ከሚያስፈልጋቸው ሌሎች ሰዎች ጋር አብረን እንደምንኖር መገንዘብ እንጀምራለን። የዕለት ተዕለትና እምብዛም ጎልቶ የማይታይ የጎን ለጎን የሕይወት ገጽታ የሌለበት፣ በቀን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የማንገናኝበት፣ ስለሚመለከተን ማንኛውም ነገር የማንጨነቅበትና በጥቃቅን ተራ ነገሮች ጭምር እርስ በርስ የማንደጋገፍበት ከዚህ ቀዳሚ ማኅበራዊ ትስስር ውጭ የሆነ አንዳችም ነገር የለም። ቤተሰብ በየቀኑ አባላቱን የሚያመሰግንባቸውንና የሚያደንቅባቸውን አዳዲስ መንገዶች ማግኘት አለበት።
በቤተሰብ ውስጥም የፍጆታ ልማዶቻችንን እንደ ገና ማጤንና የጋራ ቤታችን የሆነውን የተፈጥሮ አካባቢ በመንከባከብ ረገድ መተባበር እንችላለን። “ቤተሰብ የተቀናጀ የሥነ ምህዳር ዋና ወኪል ነው፤ ምክንያቱም ቤተሰብ በምድር ላይ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ሁለት መሠረታዊ መርሆችን፣ ማለትም የአንድነት መርሆና የፍሬያማነት መርሆን፣ በውስጡ አጣምሮ የያዘ ቀዳሚ የማኅበራዊ ሕይወት ባለቤት ነው” (294) እንደዚሁም፣ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ የችግርና የመከራ ጊዜያት ጠቃሚ ትምህርቶችን ሰጥተው ያልፋሉ። ይህም የሚሆነው፣ ለምሳሌ፣ በሕመም ጊዜያት ነው። “ሕመም ሲያጋጥም፣ በሰው ድክመት የተነሣ በቤተሰብም ውስጥ ጭምር ችግሮች ይከሰታሉ። ነገር ግን፣ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ፣ ሕመም የቤተሰብ ትስስርን ይጨምራል። … ለሰው ሕመም ሰብአዊ አዘኔታን የማያበረታታ ትምህርት ልብን ያደነዝዛል፤ የሌሎች ችግር እንዳይሰማቸው ወጣቶችን ‘ያደነዝዛቸዋል’፤ መከራን እንዳይጋፈጡና ውስንነትን እንዳይkkሙ ያደርጋቸዋል”።
በወላጆችና በልጆች መካከል የሚካሄድ የመማር የማስተማር ሂደት ይበልጥ እየተወሳሰቡ በመጡ የብዙኀን መገናኛና መዝናኛ ዘዴዎች ሊደገፍ ወይም ሊስተጓጎል ይችላል። በሚገባ ከተጠቀሙባቸው፣ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን እርስ በርስ ተራርቀው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትን በማገናኘት ረገድ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ። የቤተሰብ አባላት ዘወትር መገናኘት ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳል። ሆኖም፣ እነዚህ መገናኛ ብዙኅን አካላዊ መገኘትን ወይም ቢያንስ የሌላውን ሰው ድምጽ መስማትን የሚጠይቀውን ይበልጥ ግላዊ የሆነ ግንኙነትና ቀጥታ ውይይት ሊተኩ አይችሉም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ከማቀራረብ ይልቅ ሊያራርቁ ይችላሉ፣ ምክንያቱም በእራት ሰዓት ሁሉም ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኩ መልእክቶች ላይ እንዲያተኩር ወይም አንዱ የትዳር አጋር ተኝቶ ሌላው ግን በኮምፒዩተር መሣሪያ እየተጫወተ ሰዓታትን እንዲያሳልፍ ያደርጉታል። ይህ ደግሞ ቤተሰቦች ቁጭ ብለው ሊወያዩበትና ተጫባጭ ያልሆኑ ክልከላዎች በሌሉበትና የእርስ በርስ መስተጋብርን በሚያበረታታ መንገድ ሊፈቱት የሚገባ ጉዳይ ነው። በማናቸውም ሁኔታ፣ እነዚህ አዳዲስ የመገናኛ ዐይነቶች በሕጻናትና በዐዋቂዎች ላይ የሚያመጡአቸውን ሥጋቶች ችላ ማለት አንችልም። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ መገናኛ ዐይነቶች ከተጨባጩ ዓለም መነጠልንና አዘኔታ ማጣትን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። ይህ “ቴክኖሎጂ የሚያመጣው መገለል” የሕጻናትና የዐዋቂዎችን የግል ስፍራ በራስ ወዳድነት ጥቅሞች ለመውረር ለሚፈልጉ ተንኮለኞች በቀላሉ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ ሌላ ወላጆች ጨቋኞች መሆን የለባቸውም። ሕጻናት የሚታመኑት ወላጆች ብቻ ናቸው ብለው ሲያስቡ፣ ከሰዎች ጋር በቂ የሆነ የመቀራረብና የመብሰል ሂደት እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል። የወላጅነት ግንኙነትን ወደ ሰፊ እውነታዎች ለማስፋፋት እንዲቻል ‹‹ክርስቲያን ማኅበረሰቦች” በተለይ ከክርስቲያናዊ ሕይወት ጅማሮ ጋር በተያያዘ በሚሰጥ ትምህርተ ክርስቶስ አማካይነት “ለቤተሰቦች የማስተማር ተልእኮ ድጋፍ መስጠት ይጠበቅባቸዋል”። የተቀናጀ ትምህርትን ለማበረታታት፣ “በቤተሰብና በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ቃል ኪዳን ማደስ” ያስፈልገናል። ሲኖዶሱ “ወላጆች ልጆቻቸውን የማሳደግ ግዴታቸውን እንዲወጡ በመርዳት ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ” የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን አስፈላጊነት አጉልቶ አሳይቶአል። “…ተማሪዎች ዓለምን በኢየሱስ የፍቅር ዐይን የሚመለከቱና ሕይወት እግዚአብሔርን የማገልገል ጥሪ እንደሆነ አድርገው የሚገነዘቡ ወጣቶች ሆነው ያድጉ ዘንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን በተልእኮአቸው ማበረታታት ያስፈልጋል” ብሎአል። በዚህ ምክንያት፣ “ቤተክርስቲያን አስተምሯን የመግለጽ ነጻነትና የመምህራንን የኅሊና ድምጽ የመከተል መብት በብርቱ ትደግፋለች”።
ምንጭ፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 274-279 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ