ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “ልጆችን የመገሰጽ ጥቅም”
ብልግና የሚያስከትለውን ውጤት ሕጻናትና አዋቂዎች እንዲገነዘቡ መርዳት አስፈላጊ ነው። ራሳቸውን በሌሎች ሰዎች ቦታ እንዲያስቀምጡና ያደረሱትን በደል እንዲያውቁ ማበረታታት ያስፈልጋል። ለጠብ አጫሪነትና ለጸረ ኅብረተሰብ ድርጊቶች አንዳንድ ቅጣቶችን ማስቀመጥ ለዚህ ዓላማ በከፊል ሊያገለግል ይችላል። ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁና በሌሎች ላይ ያደረሱትን ጉዳት እንዲክሱ ሕጻናትን ማስተማር አስፈላጊ ነው። የማስተማር ሂደቱ በግላዊ ነጻነት የማደግን ፍሬ እያፈራ ሲሄድ፣ ሕጻናት በቤተሰብ ውስጥ የማደግንና እያንዳንዱ የሕንጸት ሂደት የሚጠይቀውን ነገር የመጋፈጥ ጠቀሜታ መረዳት ይጀምራሉ።
የልጆች ጥረት በሚደነቅበትና በሚታወቅበት፣ እንዲሁም ልጆች የወላጆቻቸውን ቀጣይና ታጋሽ እምነት በሚረዱበት ወቅት እርማትም ማበረታቻ ይሆናል። በፍቅር የታረሙ/የተቀጡ ልጆች እንክብካቤ ይሰማቸዋል፤ ያላቸው እምቅ ኃይል የታወቀላቸው ግለሰቦች መሆናቸውንም ይረዳሉ። ይህ ደግሞ ወላጆች የራሳቸውን ውስንነቶች በየዋህነት እንዲቀበሉና ለማሻሻል ጥረት እንዲያደርጉ እንጂ ከእነርሱ ፍጹምነትን አይጠይቅም። ሆኖም፣ ሕጻናት ከወላጆቻቸው መማር ካለባቸው ነገሮች አንዱ በቁጣ አለመነሣሣትን ነው። ያጠፋ ልጅ መታረም ቢኖርበትም፣ የራስን ተስፋ መቁረጥ ለማሳየት ሲባል ያንን ልጅ እንደ ጠላት ወይም እንደ ግዑዝ ዕቃ ማየት አይገባም። ጎልማሶችም ቢሆኑ አንዳንድ የብልግና ዐይነቶች ከወጣትነት ዕድሜ ጋር የተያያዙ የደካማነትና ውስንነት ውጤት መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋቸዋል። በቅጣት ላይ ያተኮረ አስተሳሰብ ጎጂ ነው፤ አንዳንዶቹ ድርጊቶች ከሌሎቹ ይበልጥ ከባድ መሆናቸውን ሕጻናት እንዲገነዘቡ አይረዳቸውም። ይልቁንም ወደ ተስፋ መቁረጥና ቂም መያዝ ሊመራ ስለሚችል “ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው” (ኤፌ. 6፡4፤ ንጽ. ቆላ. 3፡21)።
ሥነ ሥርዓት ተስፋ ወደ መቁረጥ የሚመራ ሳይሆን፣ ለተጨማሪ እድገት ማነቃቂያ ቢሆን ይሻላል። ሥነ ሥርዓትን እንዴት ማስቀደም ይቻላል? ሥነ ሥርዓት በልጅ ድርጊት ላይ የተጣለ ገንቢ ገደብ እንጂ በእድገት ጎዳናው ላይ የተቀመጠ መሰናክል አለመሆኑን እንዴት እናረጋግጣለን? በሁለቱ እኩል ጎጂ ጽንፎች መካከል ሚዛን ሊበጅለት ይገባል። ከእነዚህም አንዱ ሁሉም ነገር በልጁ ፍላጎት ዙሪያ እንዲሽከረከር ለማድረግ መሞከር ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚያድጉ ልጆች መብቶቻቸውን እንጂ ግዴታዎቻቸውን አያውቁም። ሌላው ልጁ የራሱን ክብር፣ ማንነትና የግል መብቶች እንዳያውቅ ማድረግ ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚያድጉ ልጆች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ በግዴታ የተዋጡና የሌሎች ሰዎችን ምኞት ብቻ ፈጻሚዎች መሆን ነው።
ነገሮችን በትእግሥት ማየት
የግብረ ገብ ትምህርት አንድ ልጅ ወይም ዐዋቂ ሰው ያልተገባ መሥዋዕትነት እንዳይከፍልና ወደ ንዴትና ማስገደድ የማያደርስ ጥረት ብቻ እንዲያደርግ ይጠይቃል። በተለምዶ ይህ የሚደረገው ተመጣጣኝ መሥዋዕትነትን ያካተቱ፣ ነገር ግን፣ በቀላሉ የሚረዱአቸውን፣ የሚቀበሉአቸውንና የሚያመሰግኑባቸውን አነስተኛ እርምጃዎች ለእነርሱ በመጠቆም ነው። ያለበለዚያ፣ ብዙ በመጠየቅ ምንም አናተርፍም። ልጁ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ከሆነ፣ እንዲያውም መልካም ነገር ማድረግን የሚያቆምበት ዕድል ሊኖር ይችላል።
የግብረ ገብ ሕንጸት አንዳንድ ጊዜ በችላ ባይነት፣ በብስጭት፣ ፍቅር በማጣት ወይም በደካማ የአስተዳደግ ተምሳሌቶች ምክንያት የሚናቅበት ሁኔታ አለ። የግብረ ገብ እሴቶች ከአሉታዊ የወላጅነት ተምሳሌቶች ወይም ከጎልማሶች ጉድለት ጋር ሊያያዙ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት፣ ወጣቶች ተመሳሳይ ነገሮችን እንዲያገናዝቡ፣ እሴቶች በጥቂት በአርያነት በሚጠቀሱ ሰዎች ውስጥ በተሻለ መልኩ እንደሚከሰቱ፣ ነገር ግን በሌሎችም ውስጥ ፍጹም ባልሆነ መልኩም ቢሆን በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚገለጹ እንዲያውቁ፣ እንዲሁም ጥርጣሬያቸው ከመጥፎ ተሞክሮ ጋር የተያያዘ ሊሆን ስለሚችል፣ ውስጣዊ ፈውስ እንዲያገኙና ከሌሎችና ከሰፊው ማኅበረሰብ ጋር ተግባብተው በሰላም ለመኖር እንዲችሉ መርዳት ያስፈልጋል።
ስለ እሴቶች ምክረ ሐሳብ በምናቀርብበት ጊዜ፣ የልጁን ዕድሜና ችሎታ ማገናዘብና ጥብቅና ግትር የሆኑ ዘዴዎችን ሳንጠቀም በዝግታ ማስኬድ ይኖርብናል። የልጅን ባሕርይ መቀየር አዝጋሚ ሂደትን እንደሚጠይቅ፣ ከዚሁ ጋር ነጻነት በራሱ የአእምሮ ብስለትን ሊያረጋግጥ ስለማይችል አቅጣጫ ማስያዝና ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ የሥነ ልቡናና የሳይንስ ትምህርቶች ያሳያሉ። ከሁኔታዎች ጋር የተያያዘ እውነተኛ ነጻነት ውስንና በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ነጻነት መልካም የሆነውን ነገር በሙሉ ግብታዊነት የመምረጥ ችሎታ አይደለም። “በፈቃደኝነት” እና “በነጻ” ድርጊቶች መካከል ያለውን ልዩነት ሁልጊዜ በበቂ ሁኔታ ማሳየት አይቻልም። አንድ ሰው አንድን መጥፎ ነገር በግልጽና በፈቃደኝነት ሊመኝ ቢችልም፣ በስሜታዊ ግፊት ወይም በደካማ አስተዳደግ ምክንያትም እንዲሁ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህን በመሰሉ ሁኔታዎች፣ ውሳኔው የሰዎችን ምኞትና ዝንባሌ የማይቃረንና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ነጻ ግን አይደለም፤ ምክንያቱም ሰዎች ያንን ክፉ ነገር መምረጣቸው አይቀርምና። ይህንንም ከአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኞች አስገዳጅ ሁኔታ ማየት ይቻላል። ሱሰኞች አደንዛዥ ዕጽ መውሰድ ሲያምራቸው፣ ዕጹን ፈጽሞ ይፈልጉታል፤ በሱስ የተጠመዱ በመሆናቸውም በዚያን ወቅት ሌላ ውሳኔ ማድረግ አይችሉም። ውሳኔያቸው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ነጻ ግን አይደለም። መምረጥ ስለማይችሉና ለአደንዛዥ ዕጾች መጋለጣቸው ሱሰኝነታቸውን ስለሚያባብሰው “በነጻነት ይምረጡ” ማለት የማይመስል ነገር ነው። ስለዚህ የሌሎች ድጋፍና የተሐድሶ ሂደት ያስፈልጋቸዋል።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 269-273 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ