የዩናይትድ ስቴትስ ጳጳሳት ፕሬዝዳንት የሞት ፍርድን ማሻሻል 'ለሰው ልጅ ህይወት ያለውን ክብር ያሳያል' ብለዋል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፌዴራል የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው 40 እስረኞች መካከል የ37ቱን የቅጣት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት ማሻሻላቸውን በቅርቡ በተሰማው ዜና ዙሪያ ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት አሁን የደረሱበት ውሳኔ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህዳር 29 ፍርደኞቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንደገና እንዲጤን እና ምሕረት እንዲደረግላቸው ካቀረቡት ጥሪ ጋር የሚስማማ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቅዱስ አባታችን ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ባቀረቡት የመልዓከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ ምዕመናን “በዩናይትድ ስቴትስ በሞት ፍርድ ላይ ላሉ እስረኞች እንዲጸልዩ” ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በዕለቱም በፍርደኞቹ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ውሳኔ እንዲሻሻል ምዕመኑ ጠንክሮ እንዲጸልይ በማሳሰብ፣ “እነዚህን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን እናስብ፥ ጌታ አምላካችን ከሞት እንዲያድናቸው ጸጋውን እንለምነው” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በብርሃነ ልደቱ ዋዜማ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዝሊካ ቅዱስ በርን በሚከፍቱበት ወቅት የሚያስጀምሩትን የኢዮቤልዩ ዓመትን በመጠባበቅ ላይ እያለን ቅዱስ አባታችን የኢዮቤልዩ ዓመትን አስመልክተው ለድሃ አገሮች የውጭ ዕዳ መሰረዝን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣትን ማስቀረትን የመሳሰሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ ያቀረቡበት ‘ስፔስ ኖን ኮንፈን-ዲት’ በሚል ርዕስ ሃዋሪያዊ ጽሁፍ መፃፋቸው ተገልጿል።
ፕረዚዳንት ጆ ባይደን የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን እስረኞች ቅጣት አሻሽለው መምጣታቸው መልካም ዜና መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህ ጉዳይ ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ ምን እንደተሰማቸው በተጠየቁበት ወቅት ፕረዚዳንት ባይደን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ያቀረቡትን ጥሪ በመስማት እና በመታዘዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ይህ ውሳኔ ለሰው ልጅ ሕይወት ክብር መስጠትን የሚያመለክት ሲሆን፥ በተመሳሳይ ጊዜ እነዚህ ግለሰቦች ለወጡበት ማህበረሰብ ኃላፊነት ስላለባቸው ሕይወታቸው ሊወሰድባቸው እንደማይገባ በመገንዘባቸው በጣም መደሰታቸውን እና ጆ ባይደን በፕረዚዳንትነት የመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ይሄንን እርምጃ በመውሰዳቸው አመስግነዋቸዋል።
በአሜሪካ ውስጥ አሁንም ድረስ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው በጣም በርካታ ሰዎች እንዳሉ በመጥቀስ እዛ የሚገኙ ካቶሊኮች የሰው ልጅ ክብርን ለማሳደግ እና የሞት ቅጣትን ለማስወገድ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ ተብለው የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ፥ ከፅንስ ጀምሮ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ የሰው ልጅ በህይወት መቆየት እንዳለበት የሚደረገው ትግል እና ጥብቅና መቀጠል እንዳለበት በመግለጽ፥ “ይህ ድምጻችንን የምናሰማበት ትልቁ ጉዳይ ይመስለኛል” ብለዋል።
በእርግጠኝነት ማንም ሰው የወንጀል ድርጊቶችን እንደማይደግፍ፥ ነገር ግን ህብረተሰቡን ሊጠብቁ የሚችሉ ስርዓቶች እንዳሉ በመጠቆም፥ በመሆኑም አረመኔያዊ የሆነውን ማለትም ወንጀለኞች ላይ የሚተላለፈውን የሞት ቅጣት ፍርድ ለማስቆም እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ አሁን በክልል ደረጃ ያንን እንደሚያደርጉ እና የሚያቀርቡት ይግባኝ በፌዴራል ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ በመጨረሻም አሁን የተወሰደው እርምጃ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታህሳስ 15 በቫቲካን ከሚያስጀምሩት የኢዮቤልዩ በዓል ጋር መገጣጠሙ ትክክለኛ ወቅት ላይ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ፥ “የዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ቃል ተስፋ እንደመሆኑ መጠን፣ እኛም ሁል ጊዜ የተሻለ ማህበረሰብ እንዲኖር ተስፋ እናደርጋለን” ካሉ በኋላ፣ ይህ ማህበረሰብ በብርሃነ ልደቱ እና በትንሳኤው የምናከብረው የክርስቶስ ታላቅ የፍቅር ስጦታ ለአለም የሚያንፀባርቅ ማህበረሰብ ነው፥ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ክስተቶች መገጣጠማቸው ጠቃሚ ነው ብለዋል።