ብጹእ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ከኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ከመጡ የክህነት ትማሪዎች ጋር ብጹእ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ከኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ከመጡ የክህነት ትማሪዎች ጋር 

የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት የክህነት ተማሪዎች ቁጥር በሁለት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩን ገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዓለም የጸሎት ቀን ለክህነት ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጸሎት እንዲደረግ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት በተመሳሳይ ቀን፥ በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት የሚገኘው የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ በአዲስ መልክ የተጀመሩት ሃዋሪያዊ ጥረቶች እና ጸሎቶች 16 አዳዲስ ሰዎች ወደ ሀገረ ስብከቱ የክህነት ትምህርት ቤት እንዲገቡ እንዳደረጋቸው በመግለጽ፥ በዚህ ዓመት ውስጥም 12 ተጨማሪ ተማሪዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ጳጳስ ሆኜ በተሾምኩበት ጊዜ ለሁለት ዓመታት ያህል፣ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ሚስጥረ ክህነት አልተደረገም። በሲመተ ጵጵስናዬ መርሃ ግብር መጨረሻ ላይ፣ በዚህ ዓመት ከካህናት ይልቅ ብዙ አባቶች ለጵጵስና እንደሚሾሙ ለምእመናን ተናግሬ ነበር” ብለዋል ብጹእነታቸው።

በዩናይትድ ስቴትስ የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የምታከብረውን 61ኛውን የዓለም የጥሪ ቀን በማስመልከት መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት በተመሳሳይ ቀን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት የካህናት ምስረታን በማስመልከት በሃገረ ስብከታቸው እየተደረገ ስላለው ጥረት አስታውሰዋል።

ብጹእ አቡነ ፈርናንዴዝ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት 16 ሰዎች ወደ ዘርአ ክህነት ትምህርት ቤት መግባታቸውን ገልጸው፥ በሀገረ ስብከቱ የካቶሊኮች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።

ሀገረ ስብከቱ በዚህ ዓመትም ወደ አሥራ ሁለት የሚጠጉ ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤቱ እንደሚገቡ እንደሚጠብቅ ጠቁመው፥ ቁጥሩ የጨመረበት ምክንያት በጸሎትና በአዲስ መልክ በተካሄደው የሃዋሪያዊ ሥራዎች ጥረት መሆኑን ጠቁመዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክት የወጣው በቅዱስ ዮሴፍ በዓል ዕለት መሆኑን ብጹእ አቡነ ፈርናንዴዝ ጠቁመው፥ ይህም ከዛሬ 11 ዓመት በፊት የተካሄደው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መንበረ ጵጵስና የተከበረበት ዕለት ነው ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ፈርናንዴስ ሲናገሩ “ዮሴፍ ተራ ሰው ነበር፥ ባል እና አሳዳጊ አባት ነበር፥ ከዛም የጌታን ጥሪ የተቀበለ ሰው ነበር ፤ እንዲሁም በዚህ ዘመንም ጌታን እሺ ብለው የሚታዘዙ ብዙ ካህናት አሉን፥ ሕይወታቸውን ለአገልግሎት የሰጡ እና ለመስዋዕትነት ራሳቸውን ያዘጋጁ ካህናት አሉን። ለሰዎች ተስፋዎችን የሚሰጡ እና የሚያቀርቡ፥ ይህም ተስፋ ከቅዱስ ቁርባን የሚመነጨውን ተስፋ ፣ በይቅርታ የሚገኘው ተስፋ ነው” ብለዋል።

“በአካባቢው ካሉ ወጣት ወንዶች ጋር በወር አንድ ጊዜ እንዲገናኙ ወጣት ካህናትን መርጠናል፥ እነዚህም ወጣቶች የሀገረ ስብከቱን የክህነት መንገድ ወይም ለሃይማኖታዊ ሕይወት ያላቸውን ጥሪ ይገነዘባሉ፣ እንዲሁም የአባ ብሬት ብራናን መጽሐፍ የሆነውን “ሺህ ነፍሳትን ለማዳን፡ ለሀገረ ስብከት ክህነት ጥሪን የመለየት መመሪያ” የሚለውን መጽሃፍ በጋራ ያነባሉ” በማለት ወጣቶች ላይ እየተሰራ ያለውን ሃዋሪያዊ ሥራ ገልጸዋል።

የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት እንደ አንድ የጥሪው አካል በማድረግ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች “ኮ ቫዲስ?” (Quo vadis?) (በአማሪኛ “ወዴት እየሄድክ ነው?” የሚል አቻ ትርጉም ያለው ሲሆን፥ ቃሉም ከዮሃንስ ወንጌል 13፡36 የተወሰደ ነው) የሚሉ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ወጣቶቹን ያነቃቃሉ።

“ወጣቶቹ ሦስት ቀናትን በጸሎት ያሳልፋሉ፣ ምስክርነቶችን በማዳመጥ፣ የክህነት ምሥረታ ምን እንደሆነ ከሚያስተምሩ ካህናት ጋር በመወያየት፣ ከጸሎት፣ ጥናትና ሥራ በተጨማሪ በወንድማማችነት መኖር ምንኛ ደስ እንደሚል የሚረዱበትንም ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህ ደግሞ በጣም ፍሬያማ ነበር”ሲሉ ብጹእ አቡነ ፈርናንዴስ ተናግረዋል።

በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በምእመናን እንዲሁም በገዳማዊያን መካከል የሚደረጉ ጸሎቶች አስፈላጊነትንም በማመላከት፥ “ሰዎች ለጥሪዎች ዓላማ መሳካት እንዲጸልዩ እና እንዲጾሙ ዘወትር እናሳስባለን” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ፈርናንዴስ በመጨረሻም “ሐሳቡ ልክ እንደ ሐዋርያት የወንጌልን ደስታ ማወጅ አለባቸው የሚል ነው፥ የእኛ የክህነት ተማሪዎች ቅዱስ አባታችን ፍራንቺስኮስ እንዳሉት ቤተክርስቲያን መሆን የሚገባትን ቤተክርስቲያን እንድትሆን እና ወደፊት የምትሄድ ቤተክርስቲያን እንድትሆን የሚያደርጉ ብሎም እውነተኛ የሚስዮናዊ ስሜት እንዲኖራቸው ከልብ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
 

20 March 2024, 14:46