የአውሮፓ ህብረት ባንዲራዎች ብራስልስ ከሚገኘው ጽ/ቤቱ ፊት ለፊት ሲውለበለብ የአውሮፓ ህብረት ባንዲራዎች ብራስልስ ከሚገኘው ጽ/ቤቱ ፊት ለፊት ሲውለበለብ   (REUTERS)

የአውሮፓ ህብረት እጩዎች ለአብሮነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ካሪታስ አሳሰበ

የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ካሪታስ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ ምርጫ እጩዎች የአውሮፓዊያንን የአብሮነት እሴት፣ ሰብአዊ እና ማህበራዊ መብቶችን እና የዓለም አቀፍ ፍትህ እሴቶችን ለሚያንፀባርቁ ፖሊሲዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስቧል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰኔ 1 እና 2/ 2016 ዓ.ም. ከሚካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ በፊት፥ ካሪታስ አውሮፓ በሚቀጥለው የአውሮፓ ፓርላማ እና ኮሚሽን የስልጣን ጊዜያት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አምስት ቁልፍ ጉዳዮችን የሚገልጽ ‘የምክረ ሃሳብ ማስታወሻ’ አውጥቷል ።

በቂ እና ሁሉን አቀፍ የሰራተኞች ገበያ እና ማህበራዊ ጥበቃ

የመጀመሪያው ምክረ ሃሳብ የ2030 የአውሮፓ የድህነት ቅነሳ ዕቅድ ላይ የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት “በቂ እና ሁሉን አቀፍ የሰራተኞች ገበያ እንዲሁም ለሁሉም ዜጎች ማህበራዊ ጥበቃ ማረጋገጥ” ለሚሉት ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል የሚል ነው።

ለዚህም ካሪታስ አውሮፓ እ.አ.አ. በ 2017 የተድነገገውን "የአውሮፓ የማህበራዊ መብቶች" 20 መርሆዎች ሙሉ አፈፃፀምን በጥንቃቄ እንዲከታተል፥ በተለይም የአውሮፓ ኮሚሽን በሚቀጥለው የአውሮፓ ፓርላማ የሥልጣን ዘመን ውስጥ በአነስተኛ የገቢ ደረጃዎች ላይ "የመመሪያ ማዕቀፍ ሀሳብ እንዲያቀርብ" ጠይቋል።

በተመጣጣኝ ዋጋ የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ

በምክረ ሃሳብ ማስታወሻው ላይ የቀረበው ሁለተኛው ጉዳይ ሁሉም የአውሮፓ ዜጎች ከፍተኛ ጥራት ያለው እና ተመጣጣኝ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብትን የሚመለከት ሲሆን፥ ይህንን መብት ማረጋገጥ የሁሉም የአውሮፓ መንግስታት ግዴታ መሆኑን ካሪታስ አውሮፓ በማስገንዘብ፥ በዚህ ዘርፍ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚናን አጉልቶ አሳይቷል። ስለዚህ የአውሮፓ ፓርላማ ይህንን ዘርፍ እንዲደግፍ ጥሪውን በማቅረብ፥ “ኮሚሽኑ ለማህበራዊ ኢንቨስትመንት 'ወርቃማ ህግ' በማውጣት ለማህበራዊ ኢንቨስትመንት እና ለትርፍ ላልሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች ምቹ የሆነ ማዕቀፍ እንዲፈጠር ሀሳብ በማቅረብ” ጥሪውን አስተላልፏል።

የስደት ፖሊሲዎች

ካሪታስ አውሮፓ በተጨማሪም የአውሮፓ ፓርላማ የአውሮፓ ህብረት እሴቶችን፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ስምምነትን፣ የሰብአዊ መብቶች እና የሁሉንም ሰዎች ክብር የሚያስቀድም የስደት እና የጥገኝነት ፖሊሲዎችን እንዲያበረታታ አሳስቧል።

ፓርላማው የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራቱ የሰዎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብትን ለማመቻቸት እና ለማስቻል እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት ሃገራት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፣ ጫናዎችን እና መድሎዎችን እንዲያቆሙ ለማበረታታት ዓለም አቀፍ አመራር እንዲያሳይ እንፈልጋለን ብሏል።

ጽሑፉ በተለይ ዓለም አቀፍ ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች “ደህንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ እና መደበኛ የሆነ የጉዞ መንገዶችን” ማበረታታት እንደሚያስፈልግ በመጠየቅ፥ በተጨማሪም ለሠራተኞች፣ ለቤተሰብ፣ ለሰብአዊ ሰራተኞች ቪዛዎች፣ ለማህበረሰብ ስፖንሰርሺፕ፣ ለስራ እና ለመኖሪያ ፈቃዶችም” ጉዞዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

“የአውሮፓ የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ የስደተኛ ሰራተኞችን መብት እና ብዝበዛን መዋጋት ማዕከሉ በማድረግ እንዲሁም የስደተኞችን ማህበራዊ ተሳትፎ እና በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሙሉ ተሳትፎን ማሳደግ አለበት” ሲል ማስታወሻው አክሏል።

“ስደተኞች በአውሮፓ ለማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ብዝሃነት የሚያበረክቱትን አወንታዊ አስተዋፅኦ እውቅና የምንሰጥበት ጊዜ ነውም” ብሏል።

ለሰብአዊ እና ለልማት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ

ካሪታስ አውሮፓ በአራተኛ ደረጃ ላይ ባስቀመጠው የውሳኔ ሃሳብ “በአውሮጳ ኅብረት የውጭ ተግባር ውስጥ በአገር ውስጥ የሚመራ ሰብዓዊ ተግባራትን እና ልማትን ማስተዋወቅ” እና “ለአካባቢው መሠረታዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀጥተኛ የሰብአዊነት እና የልማት ፈንድ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ” እንደሚገባ በመጥቀስ፥ እንዲህ ዓይነቱ የገንዘብ ድጋፍ “ለሰብአዊነት፣ ለልማት እና ለሰላማዊ የመፍትሄ ዕርምጃዎች በሚስማማ መልኩ ተለዋዋጭ እና ተስማሚ መሆን አለበት” ይላል ሰነዱ።

በደቡቡ ንፍቀ ዓለም ውስጥ ለፍትህ እና ለዘላቂ ልማት የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ስልቶች

ካሪታስ አውሮፓ በመጨረሻም የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ መሪዎች ለፍትህ እና ለዘላቂ ልማት የሚደረገውን ጥረት በደቡብ ንፍቀ ዓለም ውስጥ በንቃት እንዲደግፉ አሳስቧል። በተጨማሪም “የአውሮጳ ኅብረት አጋር አገሮችን እና የሲቪል ማህበረሰብን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሃይል ሚዛን በመጠበቅ በኩል እና ለድህነት ቅነሳ መዋቅራዊ እንቅፋት የሆኑንት ለማጥፋት በተለይ ፍትሃዊ የምግብ ስርዓት እንዲኖር፣ ኪሳራ እና ጉዳት በሚያጋጥሙ ጊዜ፣ እንዲሁም ለአየር ንብረት ጥበቃ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አለበት” ብሏል።

እንደ ካሪታስ አውሮፓ ምክረ ሃሳብ የአውሮፓ ፓርላማ ቀዳሚ በመሆን ተቋማትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ የሚመስሉ ስልቶችን እና የአጭር ጊዜ ተግባራትን ማስወገድ እንዲችሉ እገዛ ማድረ ብሎም ፍትሃዊ እና ወጥ ፖሊሲዎችን እና አሰራሮችን በተለይም በንግድ፣ በግብርና እና በስደት ዘርፍ ያሉትን ሥራዎች በማበረታታት ረገድ መሪ ሚና መጫወት አለበት ብሏል።
 

19 March 2024, 14:28