ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረመድህን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረመድህን  

ሲኖዶሳዊነት የሚጀምረው መላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከመስማት ነው!

“ሲኖዶሳዊነት የሚጀምረው ከመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከመስማት ነው። የምታስተምር ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ የምትሰማ ቤተክርስቲያን መሆን አለባት፤ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደሚያስታውሰን ሁሉም ምእመናን በአጠቃላይ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ናቸው ስለሆነም ሁሉንም የቤተክርስቲያን አባላት ማማከር አስፈላጊ ነው ።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የ53ኛ መደበኛ የጳጳሳት ጉባኤ የሰበካዎች የሲኖዶስ ውይይት ውጤት የሆነውን የተጠናቀረ ጽሁፍ የሲኖዶስ ሀገርአቀፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት በክቡር አባ ገብረመስቀል ሽኩር ቀረበ።

ሀምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ብጹዓን ጳጳሳት፤ የሀገረስብከት ተወካዮች፤ የተለያዩ ማህበራት እና እንቅስቃሴ ተወካዮች እንዲሁም የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ክቡር አባ ገብርኤል ወ/ሃና የሲኖዶስ ኮሚቴውን በመወከል ቤተክርስቲያን በሲኖዶስ እንቅስቃሴ ላይ ያደረገችውን ተሳትፎ አብራርተዋል። እንቅስቃሴው ከጥቅምት ወር ጀምሮ ላለፉት 8 ወራት የቆየ ሲሆን የጳጳሳት ጉባኤ የሲኖዶስ እንቅስቃሴ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲዳረስ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሲኖዶስ ቢሮ እና የቢሮውን አስተባባሪ በመሾም የተጀመረ ሲሆን በመቀጠልም በሃገር አቀፍ ደረጃ 8 አባላትን የያዘ የሲኖዶስ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክቡር አባ ገብርኤል ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተደረጉ የምክክር መድረኮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን እንዲሁም ውይይቶች፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በከፍተኛ የሃይማኖት ምሁራን ለብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የሃገረስብከት ተወካዮች እና ለሲኖዶስ ተወካይ ምዕመናን መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የሲኖዶስ ሀገርአቀፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት በክቡር አባ ገብረመስቀል ሽኩር የቀረበው ከየሀገረስብከቶች የተሰበሰቡ ባለ 10 ገጽ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ በሀገር አቀፍ የሲኖዶስ ኮሚቴ ተጠናቅሮ የቀረበውን ጽሁፍ አቅርበዋል። የቀረበው ጽሁፍ የመጀመሪያ ረቂቅ ሲሆን ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምንነት፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎችን የያዘ ነው። ጽሁፉ በ 16 የተለያዩ ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን በያንዳንዱ ሁኔታ ያሉትን ተግዳሮቶች፤ ጥያቄዎች እናም ተያይዘው የሚመጡ እድሎችን ወደተግባር የሚውሉበት ሀሳቦች ተዳሰዋል። የአምልኮ ስርዓት፣ ጥሪ፣ ገዳማውያን፣ ወጣቶች፣ ካታኪስቶች፣ መደማመጥ እና መነጋገር፣ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ በጽሁፉ ከተነሰሱት ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

ክቡር አባ ገብረመስቀል “ውይይት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጋር በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ስር” የሚለውን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሃሳብ ውይይት “በሀገርስብከት ከጳጳሱ ጋር በጳጳሱ ስር ፤ በቁምስና ከቆሞሱ ጋር በቆሞሱ ስር እንዲሁም በቤተሰብ ከአባወራ ጋር በአባወራ ሥር አውርደን መስራት አለብን” ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ይህንን ጽሁፍም ለወደፊት አቅጣጫ መሰረት በማድረግ የምትጠቀመው በመሆኑ የተጠናቀረው ጽሁፍ ወደሮም ከመላክ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ወንጌልን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል። የቀረበው ጽሁፍ ላይ መጨመር ያለባቸው፤ መስተካከል ያለባቸው ሃሳቦች ከተሳታፊዎች ተስጥቷል።

የሀገር አቀፍ የሲኖዶስ አባል የሆኑት ሲስተር ሉጂና ገብረወልድ “ሲኖዶስ ካቶሊካዊ ማንነታችን ያንጻል፤ ይህ ሲኖዶስ ለአንዲት ቤተክርስቲያን እድገት መታነጽ ትልቅ እድል ነው” በማለት በሃሳብ የገለጽነው ሁሉ ወደተግባር ማዋል የሁሉም ካቶሊክ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ሲኖዶሱ የብዙዎችን ድምጽ የተሰማበት እና የእግዚአብሔርን ድምጽ በመስማት ወደፊት ለስብከተ ወንጌል ምን የተሻለ መስራት እንድምንችል አቅጣጫ የሚያሳይ ውይይት መሆኑ ተገልጿል። የተነሱት ሃሳቦች ወደጋራ ተልዕኳችን መንገድ የሚመሩን ሊሆን የሚገባ መሆን እንዳለበት እና የሚታቀዱት ሥራዎች ሁሉ በህብረት፤ በተሳትፎ እና በጋራ ተልዐኮ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምንጭ፡ ከኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባሄ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ!

22 July 2022, 14:56